አዳማ፣ ህዳር 20 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ ለኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሥራ መሪዎች የኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ (ERP) ሥልጠና በአዳማ ኃይሌ ሪዞርት እየተሰጠ ነው ።

“ኤክሲድ አይቲ ሲስተምስ” ከሚባል ኩባንያ ጋር በመተባበር ከህዳር 20 ቀን ጀምሮ ለሁለት ቀናት የተዘጋጀውን ሥልጠና የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ መልእክት በማስተላለፍ ከፍተዋል።
በዚሁ ወቅት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንደተናገሩት፣ የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት፣ ሀብት በአንድ የመረጃ ቋት ውስጥ መዝግቦ ለማስተዳደር፣ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ እና በአጠቃላይ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት ሥልጠናው መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ኢ አር ፒን በተሟላ መልኩ ለመተግበር የሥራ መሪዎች ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ወ/ሮ የሺእመቤት፣ በኮርፖሬሽኑ በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የኢ አር ፒ ሲስተም በሚፈለገው ደረጃ አለመተግበሩን ተናግረዋል።
ይህም የሆነው ፈጻሚው አካልና ሲስተሙ ባለፉት ሰባት ዓመታት በሚጠበቀው ልክ ስላልተገናኙ መሆኑን አስረድተዋል።
በሥልጠናው ላይ የተገኙት አቶ ፍቅሬ ታደገኝ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሰብስደሪ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ተጠባባቂ ዳይሬክተር በበኩላቸው፣ በኮርፖሬሽኑ የኢ አር ፒ ሥርዓት የተዘረጋ ቢሆንም በሁሉም ሥራዎች ላይ ተግባራዊ ባለመደረጉ ክፍተት መፈጠሩን ጠቁመዋል።
አክለውም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረቢያ ደረጃዎችን (IFRS) በመተግበር የኮርፖሬሽኑን ሒሳብ በወቅቱ ለመዝጋት ኢ አር ፒን መጠቀም ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበው፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ አሠራርን ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል።
በዕለቱ “Change Management for Leadership” በሚል ርዕስ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፣ ሥልጠናውን የሰጡት ወንድወሰን ሙሉጌታ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዲጂታላይዜሽንና መሰረተ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ናቸው።
በሥልጠናው ስለ ኢ አር ፒ ምንነትና ጠቀሜታ እንዲሁም ለውጥ በዲጂታላይዜሽን ዘመን ምን እንደሚመስል ተብራርቷል።

ለውጥን በተቋም ውስጥ ለማስረጽ የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ያሉት ዶክተር ወንድወሰን፣ ኢ አር ፒ የሰው፣ የቴክኖሎጂና የሂደት (process) ጥምረት በመሆኑ አንዱ ቢጎድል ሲስተሙ ይስተጓጓላል ብለዋል።
የተግባር ሥልጠና የተካተተበት ይህ መርሐ ግብር በነገው ዕለትም ይቀጥላል።
EXCEED IT SYSTEMS በሚባል የሶፍትዌር ማበልጸግና ትግበራ ላይ በተሰማራ ኩባንያ አማካኝነት በኮርፖሬሽኑ የኢ አር ፒ ሲስተም ከተተገበረ ሰባት ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን፣ በቀጣይ ሲስተሙን በሚፈለገው ደረጃ ለማስቀጠል የሚያስችሉ 14 ሞጁሎች ተዘጋጅተዋል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!







