አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2018(ኢዜአ)፦ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምርትና ምርታማነታቸው የተረጋገጡ ምርጥ ዘሮችን በስፋት እያበዛ መሆኑን በኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የአርዳይታ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
ኮርፖሬሽኑ እንደ ሀገር በግብርናው ዘርፍ የተያዘውን ግብ ዘላቂ በማድረግ ሁሉን አቀፍ ዕድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ በተግባር እየተወጣ መሆኑ ተመላክቷል።
በኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የአርዳይታ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ተወካይ ሃላፊ አዲሱ ጋረደው ምርጥ ዘርን በብዛትና በጥራት ማምረት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የስንዴ፣ የጎመን እና የገብስ ምርጥ ዝርያዎችን እያባዛ በመላው ሀገሪቱ ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ቅድመ መስራች፣ መስራች እና የተመሰከረለት የተባሉ ምርጥ ዘሮችን ከ 3ሺህ 100 ሄክታር መሬት ላይ እያባዛ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከ 90 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት ማቀዱንም ተናግረዋል።
ሀገር አቀፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ኮርፖሬሽኑ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።
በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የሚባዛው ምርጥ ዘር ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የአየር ንብረትና የአፈር ዓይነት ጋር የሚስማማ በመሆኑ የምርት ብክነትን በመቀነስ የሰብል ጥራትን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ የሚያሰራጫቸው ምርጥ ዘሮች ከፍተኛ ምርት በማስገኘት የአርሶ አደሩን የምርት መጠንና ጥራት የሚያሳድጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምርጥ ዘር የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ዋነኛው መሠረት መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአርዳይታ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከፍተኛ የሜካናይዜሽን ባለሙያ አቶ ሠራዊት ጅማ በበኩላቸው፤ የምርት ስብሰባ ሂደቱ በ13 ኮምባይነሮች በመታገዝ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የምርት ብክነትን ለመከላከልና የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ የግብርና ግብዓቶችንና ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን በማቅረብ እንዲሁም የተቀናጀ የሜካናይዜሽን አገልግሎት በመስጠት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ኮርፖሬሽኑ በ2017/18 የምርት ዘመን ለማባዛት ያቀደው 460 ሺህ ኩንታል ዘር መሆኑም ታውቋል።




