አዲስ አበባ፣ ህዳር 9 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ተገመገመ።
በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ህዳር 9 ቀን 2018 ዓ.ም የተደረገውን ግምገማ የመሩት የሆልዲንጉ ከፍተኛ አመራር ወ/ሮ አስማ ረዲ ናቸው።
በግምገማው ወቅት ኮርፖሬሽኑ በምርጥ ዘር አቅርቦት፣ በደን ውጤቶችና ቅባት እህሎች ኤክስፖርት ዝግጅት አበረታች ተግባራትን ማከናወኑ ተገልጿል።
ይሁንና የግብርና ግብዓትና እርሻ መሣሪያዎች ሽያጭ አፈጻጸምን ለማሻሻል በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ በተሰጠው ግብረ መልስ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሆልዲንጉ ከፍተኛ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጥቂት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ መሆኑን ያስታወቁት ወይዘሮ አስማ፣ ሆልዲንጉ የኮርፖሬሽኑን አፈጻጸም ለማሻሻል የሚያስችሉ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም የተቋሙ አዲስ አመራሮች የኦፕሬሽን ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ተረድተው ስትራቴጂካሊ መምራት መቻላቸው የሚደነቅና የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ በበኩላቸው፣ የኮርፖሬሽኑን ቀጣይነትና ውጤታማነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ጥናትን መሰረት በማድረግ እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
በዕለቱ ከሆልዲንጉ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!








