አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7/2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- “ብሔራዊ ጥቅም እና የጂኦስትራቴጂ ቁመና” ርዕሰ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ተወያዩ።

በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት የተካሄደውን የውይይት መድረክ የመሩት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ በ”ብሔራዊ ጥቅምና የጂኦስትራቴጂ ቁመና” ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተዘጋጀን የመነሻ ሰነድ አቅርበዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በዚህ ወቅት ባደረጉት ገለጻ፣ ብሔራዊ ጥቅም የሀገራዊ ህልውና፣ ደኅንነትና ብልጽግና ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
አክለውም የብሔራዊ ጥቅምና የጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና አጀንዳ የሀገር፣ የሕዝብና የትውልድ አጀንዳ መሆኑን ገልጸው፣ አሁን ባለንበት ሁኔታ የባህር በር ጥያቄ ወደ አጀንዳነት እየተቀየረ ነው ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት አለበት ያሉት ወ/ሮ የሺእመቤት፣ ለተልዕኮው መሳካት የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ሠራተኞች ግምባር ቀደም ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በመጨረሻም “ለሀሰት ትርክትና ፕሮፓጋንዳ እጅ ሳንሰጥ አንድ ሆነን ሀገራችንን ወደተሻለ የእድገት ምዕራፍ ማሸጋገር አለብን” ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ውስጣዊ አንድነትን ይበልጥ በማጠናከር ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በዕለቱ ከሠራተኞች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምላሽ ሰጥተዋል።



