ኢግሥኮ ምን ዓላማዎችን እንዲያሳካ ተቋቋመ? ምርትና አገልግሎቶቹ ምንድናቸው? የእስካሁኑ የልማት ጉዞው ምን ይመስላል?
ተከታዩ ፕሮፋይል ይህንኑ በአጭሩ ያስቃኛል።
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) – አጭር መግለጫ/ፕሮፋይል
ምስረታ
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) በግብርናው ዘርፍ ከ30 እስከ 40 ዓመት ድረስ በተናጠል አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ አምስት ነባር ድርጅቶችን (የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት፣ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅራቢ ድርጅት፣ የእርሻ መሣሪያዎችና የቴክኒክ አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር፣ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ድርጅት እና የተፈጥሮ ሙጫ ምርትና ገበያ ድርጅት) በማዋሃድ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 368/2008 መሠረት ታህሳስ 2008 ዓ.ም የተቋቋመ መንግሥታዊ የልማት ድርጅት ነው፡፡
ተጠሪነት
በግሉ ዘርፍና በተደራጁ ማኅበራት የማይሸፈኑ የገበያ ክፍተቶች ውስጥ የድርሻውን በመውሰድ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ የሚገኘው ኮርፖሬሽኑ ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሲሆን፣ በሥራ አመራር ቦርድ ይመራል፡፡
የተቋቋመበት ዓላማ
የተቋቋመበት ዓላማ ለግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት አስተዋጽዖ የሚያደርጉ እና ለዘመናዊ እርሻና ለአግሮ ኢንዱስትሪ መስፋፋት መሠረት የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እና ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ልማትና ዕድገትን ለማፋጠን ነው፡፡
የተቋቋመበት ዝርዝር ዓላማዎቹም የሚከተሉት ናቸው፦
፩/ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎችን ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ገዝቶ ለገበያ ማቅረብ፤ ማዘጋጀት፤ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎችን የገበያ ዋጋ የማረጋጋት ተግባራትን ማከናወን፤
፪/ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት፣ የእርሻና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን የጥገና አገልግሎት፣ የእርሻ መሣሪያዎችንና የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎችን የኪራይ አገልግሎት በክፍያ መስጠት፤
፫/ የእርሻ መሣሪያዎችንና መለዋወጫዎችን፣ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን እና አግሮ ኬሚካሎችን ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ገዝቶ ለሽያጭ ማቅረብ፤
፬/ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች አጠቃቀም እንዲለመድ አስፈላጊውን ትምህርት መስጠት፤ ስለ እርሻ መሣሪያዎች አያያዝና አጠቃቀም የምክር አገልግልት መስጠት፤ የቴክኒክ ሞያ ማሻሻያ ሥራ ላይ ሥልጠና መስጠት፤
፭/ የተፈጥሮ ሙጫ ምርት መሰብሰብ፣ መግዛት፣ እሴት መጨመር፣ ማዘጋጀት፤ ሌሎች ከደን ውጤቶች የሚመረቱ ምርቶችን ማምረት፣ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያዎች ማቅረብ፤
፮/ የእርሻ መሬት ልማት ጥናትና ዲዛይን፣ የእርሻ መሬት ቅየሳ፣ ምንጣሮና ማስተካከል፣ የውኃ ተፋሰስና የመስኖ ሥራ እንዲሁም ከእርሻ መሬት ልማት ጋር የተዛመዱ ሥራዎችን ማከናወን፤
፯/ የአዳዲስና ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን አዋጪነት ጥናት፣ የዲዛይን ዝግጅት፣ የቴክኖሎጂ መረጣና ድርድር፣ የተከላና የኮሚሽኒንግ እንዲሁም የምርምር ሥራዎች እንዲካሄዱ ማድረግ፤
፰/ አቅሙ ካላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጪ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር የግብርና የማምረቻ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎች ዲዛይንና የማምረት ሥራዎች በሀገር ውስጥ እንዲከናወኑ ማድረግ፤
፱/ ለመስኩ የሚፈለገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በሚፈለገው ዓይነት፣ መጠንና ጥራት ለማፍራት እንዲቻል ከሚመለከታቸው የትምህርት፣ የምርምርና የሥልጠና ተቋማት ጋር በመተባበር መሥራት፤
፲/ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በሚሰጠው አቅጣጫ ላይ በመመስረት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ተወዳዳሪና አትራፊ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ እገዛ የሚያደርጉለትን የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና የዘመናዊ አስተዳደር ግብዓቶችን ለማግኘት የሚያስችለውን (ኢንቨስትመንት መሳብንም ሆነ በኢንቨስትመንት መሳተፍን ጨምሮ) ጥናት በማካሄድ ሲፈቀድ ተግባራዊ ማድረግ፤
፲፩/ የተለያዩ የአዝዕርት፣ የአትክልት፣ የፍራፍሬና የመሳሰሉት ቅድመ መሥራች፣ መሥራችና የተመሠከረለት ዘር ማባዛት፣ ማበጠርና ማዘጋጀት፣ እንደ አስፈላጊነቱም ቅድመ መሥራች ዘሮችን ከውጭ አገር በማስመጣት ማስመረት ወይም መሸጥ፣ ተረፈ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ፤
፲፪/ በግብርና ግብዓት አቅርቦት፣ በእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት፣ በእርሻ መሣሪያዎች ጥገና፣ በተፈጥሮ ሙጫ ምርትና ገበያ፣ በሜካናይዜሽን አገልግሎትና በተዛማጅ ሥራዎች ዙሪያ ምርምር በማካሄድ የተሻሻሉትን ተግባራዊ ማድረግ፣ በውጤቱም ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ፤
፲፫/ የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በሚሠጠው አቅጣጫ መሠረት ቦንድ መሸጥ፣ ዋስትና ማስያዝ፣ ከሀገር ውስጥና ከውጪ የገንዘብ ምንጮች የብድር ውል መደራደርና ሲፈቀድ መፈራረም፤
፲፬/ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተዛማጅ ሥራዎችን ማከናወን ናቸው፡፡
የኮርፖሬሽኑ ተልዕኮ፣ ራዕይ እና እሴቶች
ተልዕኮ
ለግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት አስተዋጽዖ የሚያደርጉ፣ ለዘመናዊ እርሻና ለአግሮ ኢንዱስትሪ መስፋፋት መሠረት የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እና ግብዓቶችን ተደራሽ በማድረግና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ሀገራዊ ልማትና ዕድገትን ማፋጠን፡፡
ራዕይ
በግብርና ግብዓት አቅርቦት እና በሜካናይዜሽን አገልግሎት በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ተወዳዳሪ ተቋም መሆን፡፡
እሴቶች
• ተዓማኒነት
• ግልጽነት
• ቅንነት
• ቁርጠኝነት
• የጋራ ተጠቃሚነት
• ማኅበራዊ ኃላፊነት
የአንድ መስኮት አገልግሎት
የአንድ መስኮት የተቀናጀ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ኮርፖሬሽኑ፣ በተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ የሚዘልቁ የግብርና ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ በተጨማሪም ለግብርና መዘመንና ለምርታማነት እድገት የላቀ አስተዋጽዖ ያላቸውን ግብዓቶች (ምርጥ ዘር፣ ጠጣርና ፈሳሽ ማዳበሪያዎች፣ አግሮኬሚካሎች) እንዲሁም የእርሻ መሣሪያዎችን ከእነተቀጽላቸው እና መለዋወጫቸው በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ያቀርባል፡፡
ከዚህ ባሻገር ኮርፖሬሽኑ ለደንበኞቹ እየሰጠ የሚገኘውን የአንድ መስኮት አገልግሎት የተሟላ ለማድረግ የምክር፣ የቴክኒክና ሞያ ሥልጠና፣ የዘር ብጠራ፣ የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት እና የተሽከርካሪዎች ጥገና አገልግሎቶችን በዋና መ/ቤት እና በቅርንጫፎች ተደራሽ በማድረግ ላይ ነው።
የግብርና ግብዓቶችና የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት እና አገልግሎቶች
ምርጥ ዘር
በሀገር ደረጃ በምርጥ ዘር አቅርቦት ፋና ወጊ የሆነው ኮርፖሬሽኑ፣ በተለያዩ ክልሎች የራሱን ስድስት የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ጣቢያዎችን በማቋቋም እንዲሁም በሰፋፊ የመንግሥትና የግል እርሻዎች እና በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮች ማሳ በኮንትራት በመስራት በአጠቃላይ ከ20 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የ22 ሰብሎችን 90 ዝርያዎች እያባዛ በዓመት ከ450 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ለተጠቃሚዎች እያቀረበ ይገኛል፡፡
ይህም በሀገር ደረጃ ካለው የምርጥ ዘር ፍላጎት ውስጥ 30 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ እንዲያሟላ አስችሎታል፡፡
በአጠቃላይ ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ክልሎች በአገኛቸው ተጨማሪ የእርሻ መሬቶች ዘር እያባዛ ሲሆን፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ሰብሎችን ለማምረትም ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ማዳበሪያ፣ አግሮኬሚካልና የእንስሳት መድኃኒት
ኮርፖሬሽኑ በሀገር ውስጥ ብቸኛ የጠጣር የአፈር ማዳበሪያ አስመጪ ሲሆን፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያዎች (በጠጣርና በፈሳሽ መልክ)፣ ጸረ አረም፣ ጸረ ነፍሳትና ጸረ ፈንገስ ኬሚካሎች እና የእንስሳት መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ላይ ነው፡፡
የእርሻ መሣሪያዎች
ኮርፖሬሽኑ ለሀገሪቱ መልክአ ምድር እና የአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ ዘመናዊና ጥራት ያላቸውን ትራክተሮችና ተቀጽላዎች/implements – ማረሻ፣ መከስከሻ፣ መስመር ማውጫ፣ ዘር መዝሪያ፣ ማዳበሪያ መበተኛ…/፣ ኮምባይን ሀርቨስተር፣ የኮንስትራክሽን እና የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎች፣ የመስኖ ፓምፕ ወዘተ ያቀርባል።
የሜካናይዜሽን አገልግሎት
የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎትን በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ የሚታወቀው ኮርፖሬሽኑ በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች፣ ከፊል አርብቶ አደሮች፣ ባለሃብቶች፣ የልማት ድርጅቶች ወዘተ ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ የሚዘልቁ የግብርና ሥራዎችን ያከናውናል፡፡
የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል
ኮርፖሬሽኑ ለካፒታል ፕሮጀክት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የዘር ማበጠሪያና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው ክልሎች የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል ለማቋቋም እየሠራ ነው፡፡ ለአብነት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ የአስገነባውን ግዙፍ ማዕከል መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ይህን መሰል ማዕከል በሌሎች ክልሎችም ለማስፋፋት የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡
የእርሻ መሣሪያዎችን የመገጣጠም ሥራ
የግብርና ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት ረገድ ኮርፖሬሽኑ አዳዲስ የእርሻ መሣሪያዎችን ታዋቂ ከሆኑ የአውሮፓ እና የቻይና አምራች ኩባንያዎች በማስመጣት እና ባለው ወርክሾፕ በሂደት ሙሉ በሙሉ ገጣጥሞ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና መሥራት የሚችልበትን ስምምነት እያደረገ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ተቋሙ የእርሻ መሣሪያዎችን በከፊል የመገጣጠም ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
የተፈጥሮ ሙጫ ምርቶች
ኮርፖሬሽኑ የተፈጥሮ ሙጫ ምርቶች የሆኑትን ሙጫ፣ እጣን፣ ከርቤና አበከድ በማምረትና በግዥ በማሰባሰብ አበጥሮ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ጭምር በማቅረብ በዓመት በሚሊየን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ላይ ነው፡፡
ተቋሙ እነዚህን ምርቶች የሚሰበስበው በዘርፉ ከተሰማሩ ማኅበራትና ግለሰቦች በግዥ መልክ ሲሆን፣ ምርቶቹ በአብዛኛው በትግራይ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች ቆላማ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡
የደረቅ ጭነት ትራንስፖርትና የተሽከርካሪዎች ጥገና አገልግሎቶች
ኮርፖሬሽኑ ከባድ ተሽከርካሪዎችን በማሰማራት ለውስጥ እና ለውጭ ደንበኞች የግብርና ግብዓቶችንና የእርሻ መሣሪያዎችን እንዲሁም ሌሎች የደረቅ ጭነቶችን የማጓጓዝ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በሌላ በኩል ለውስጥ እንዲሁም ለተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት ደንበኞች የተሽከርካሪዎች የቅድመ መከላከል (Preventive Maintenance Service) እና የብልሽት ጥገና አገልግሎት (Maintenance Service) ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም ለከባድ እና ቀላል ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ የቴክኒክ ብቃት ማረጋገጫ ምርመራ/ቦሎ/ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
የዓመታዊ ሽያጭ፣ ትርፍና የተፈቀደ ካፒታል እድገት
ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ዓመታት በሀገራዊ የግብርና ዘርፍ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ እና ለሦስተኛ ጊዜ በአዘጋጀው የተቋሙ ስትራተጂክ ዕቅድ (ከ2016- 2020 ዓ.ም) እየተመራ ውጤትን መሰረት ያደረገ የዕቅድ አፈጻጸም ምዘና ሥርዓትን (BSC) የለውጥ መሣሪያ አድርጎ ወደ ሥራ በመግባቱ፣ በየዓመቱ በIFRS ደረጃዎች መሰረት በወቅቱ ሒሳብ በመዝጋቱና በማስቀጠሉ እንዲሁም የISO 9001፡2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን በመተግበሩ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡
በዚህም ዓመታዊ ገቢውን ሲቋቋም ከነበረበት ከ1.4 ቢሊዮን ብር በ2016 በጀት ዓመት ወደ 10.76 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከታክስ በፊት ትርፉን ከ45.6 ሚሊዮን ብር በ2016 በጀት ዓመት ወደ 1.8 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል፡፡
ከዚህ የተነሳ ኮርፖሬሽኑ በየዓመቱ ምርቱን እያሳደገ እና አገልግሎቶቹን ይበልጥ ተደራሽ እያደረገ በመቀጠሉ እንዲሁም ትርፋማ ሆኖ በመዝለቁ ምክንያት ሲቋቋም በመንግሥት የተፈቀደለትን 2.44 ቢሊዮን ብር ካፒታል በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በማሟላት አሁን ላይ የተፈቀደ ካፒታሉን ወደ 7 ቢሊዮን 564 ሚሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎም የተቋሙን ካፒታል በድጋሚ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ማኅበራዊ ኃላፊነት
ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ኮርፖሬሽኑ በየዓመቱ በአማካይ ለ2500 ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ እድል እየፈጠረ ሲሆን፣ ከሚያገኘው ትርፍ ላይም በየዓመቱ ለማኅበራዊ አገልግሎት በጀት በመመደብ በምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት አካባቢዎች ለሚገኘው ማኅበረሰብ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በመንግሥት ለሚቀርብለት የተለያዩ የድጋፍ ጥሪዎች እና የስፖንሰርሺፕ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል፤ አሁንም ድጋፍ ማድረጉን ቀጥሏል፡፡
በዚህ መሰረት በበጎ አድራጎት ሥራዎች በእርሻ ልማቱ አካባቢዎች ለሚገኘው ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት በመገንባት፣ መብራት በማስገባት፣ የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች በማደስ፣ ለችግረኛ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን በመለገስ፣ መንገድ በመሥራት እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ችግኞችን በመትከል፣ ደም በመለገስ ወዘተ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡
በተመሳሳይ ለአካባቢው አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በአምስት በመቶ የዋጋ ቅናሽ ምርጥ ዘር በማቅረብ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ያለውን አለኝታነት በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡
እውቅና እና ሽልማት
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ በሚያቀርባቸው የግብርና ግብዓቶችና በሚሰጣቸው የተቀናጁ አገልግሎቶች በገበያ ውስጥ ተመራጭ ስለመሆኑ የረጅም ዓመት ደንበኞቹ ምስክሮች ናቸው፡፡
ለዚህም እንደ ማሳያ በ2017 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት 12ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ውድድር ህዳር 20 ቀን 2018 ዓ.ም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በተገኙበት በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተካሄደ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ የአድናቆት የምስክር ወረቀት/Honorary Certificate/ ማግኘቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በተመሳሳይ ኮርፖሬሽኑ በግብርናው መስክ በአስመዘገበው አበረታች ውጤት የአቢሲኒያ ዓለም አቀፍ የጥራት ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለኢንደስትሪ ሽልማት ካጫቸው ከ57 ሺህ በላይ አምራችና አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት፣ የግል እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ ከተመረጡ 50 ተቋማት አንዱ በመሆን መጋቢት 2015 ዓ.ም የመጀመሪያውን የኢንደስትሪ የከፍተኛ ክብር ሽልማት ተቀዳጅቷል፡፡
በተጨማሪም በታማኝ ግብር ከፋይነት ለሦስተኛ ጊዜ በፕላቲነም ደረጃ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እጅ ሽልማት ተቀብሏል፡፡
ከዚህ ባሻገር በ2015/16 የምርት ዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ በስንዴ ልማት ከሀገራዊ ፍላጎት እስከ ውጭ ገበያ አቅራቢነት በመሸጋገር ሂደት ለአበረከተው የላቀ አስተዋጽዖ እንዲሁም በ2016/17 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ግዥ፣ አቅርቦትና ሥርጭት እንዲሳለጥ ለተወጣው ከፍተኛ ድርሻ የእውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀቶችና ዋንጫ አግኝቷል፡፡
በሌላ በኩል የኮርፖሬሽኑ የወንዶች የመረብ ኳስ ቡድን የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በ2015 እና በ2017 ዓ.ም በአዘጋጀው የስፖርት ውድድር ሻምፒዮን በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
አደረጃጀት
የአርሶና አርብቶ አደሩ አለኝታ የሆነው የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን /ኢግሥኮ/ በመንግሥት የተሰጠውን ተልዕኮ ከመወጣት አኳያ በአራት ኮርፖሬት ዘርፎች (ግብርና ግብዓት ምርትና አቅርቦት ዐቢይ ዘርፍ፣ እርሻ መሣሪያዎችና የግብርና ውጤቶች አቅርቦት ዐቢይ ዘርፍ፣ ኮርፖሬት የሀብት አመራር ዘርፍ እና ኮርፖሬት ፋይናንስ ዘርፍ)፣ ዓላማ አስፈጻሚ በሆኑ አምስት የኦፕሬሽን ዘርፎች፣ በ14 ድጋፍ ሰጪ የሥራ ሂደቶች እንዲሁም በበርካታ ቅርንጫፎችና ጣቢያዎች በተደራጀ መዋቅር ከ1,600 በላይ ቋሚና ኮንትራት ሠራተኞችን ይዞ ግብርናን ለማዘመን እየሠራ ይገኛል፡፡
የዘርፎች አድራሻ እና የሚሰጡት አገልግሎት
ምርጥ ዘር፣ የዘር ብጠራ አገልግሎት፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ አግሮኬሚካል፣ የእንስሳት መድኃኒትና የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎች ካስፈለግዎ
የግብርና ግብዓት ምርትና አቅርቦት ዐቢይ ዘርፍ
ስልክ፡- +251-11-440-3610
ፋክስ፡- +251-11-442-3613
ለምርጥ ዘር አንዲሁም ለዘር ብጠራ አገልግሎት
የምርጥ ዘር አቅርቦት ዘርፍ
ስልክ፡- +251-11-661-2266
ፋክስ፡- +251-11-618-6123
ለአፈር ማዳበሪያ፣ አግሮኬሚካል፣ እንስሳት መድኃኒትና የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎች
የግብርና ግብዓት አቅርቦት ዘርፍ
ስልክ፡- +251-11-442-5623/28
ፋክስ፡- +251-11-442-5622
የእርሻ መሣሪያዎች፣ የጭነት ተሽከርካሪዎችና ጥገና፣ የግብርና ውጤቶች ሽያጭና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ቢያስፈለግዎ
የእርሻ መሣሪያዎችና የግብርና ውጤቶች አቅርቦት ዐቢይ ዘርፍ
ስልክ፡- +251-11-442-5012
ለአስተማማኝና ዘመናዊ የእርሻና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ሽያጭና ኪራይ፣ መለዋወጫ እንዲሁም የቴክኒክ ሥልጠና አገልግሎት
የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት ዘርፍ
ስልክ፡- +251-11-442-3438
ፋክስ፡- +251-11-442-0895
ለመሬት ዝግጅት፣ ምንጣሮ፣ መሬት ድልዳሎ፣ ለእርሻ ሥራ፣ ሰብል ለመሰብሰብና ለመውቃት እንዲሁም ለዕጣን፣ ሙጫ፣ ከርቤና አበከድ አቅርቦት
የግብርና ውጤቶች ሽያጭና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ
ስልክ፡- +251-11-442-5012
ለደረቅ ጭነት አገልግሎት እንዲሁም ለእርሻ መሣሪያዎችና የቀላል ተሽከርካሪዎች ጥገና
የተሽከርካሪዎች አስተዳደርና ጥገና ዘርፍ
ስልክ፡- +251-11-470-8470
ፋክስ፡- +251-11-442-0434
የሰው ሀብት፣ የግዥና ንብረት እንዲሁም የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ መረጃዎች ቢያስፈልግዎ
ኮርፖሬት የሀብት አመራር ዘርፍ
Tel: +251-11-442-1213
Fax: +251-11-442-2314
ፋይናንስ ነክ መረጃዎች ቢያስፈልግዎ
ኮርፖሬት ፋይናንስ ዘርፍ
Tel: +251-11-470-9093
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!