
አሶሳ፣ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እያካሄደ የሚገኘውን የልማት ሥራ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን የክልሉ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን አስታወቁ።ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ያስታወቁት፣ በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም የተመራ የልዑካን ቡድን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው በአነጋገሩበት ወቅት ነው። ውይይቱ በዋነኛነት ያተኮረው ኮርፖሬሽኑ ለክልሉ ባቀረበው የበቆሎ ምርጥ ዘር ማባዣ የእርሻ መሬት ጥያቄ እና በተፈጥሮ ሙጫና እጣን ምርቶች አቅርቦት ላይ ነው።

በዚህ ወቅት አቶ አሻድሊ፣ ኮርፖሬሽኑ በ2013 ዓ.ም ለክልሉ አቅርቦ ለነበረው የምርጥ ዘር ማባዣ የእርሻ መሬት ጥያቄ ምላሽ በመስጠት መሬት መፍቀዳቸውን አስታውሰው፣ ይሁንና ኮርፖሬሽኑ የተፈቀደው መሬት ለበቆሎ ምርጥ ዘር እንደማይስማማ በመግለጽ ተለዋጭ መሬት መጠየቁን ተናግረዋል።
በዚህ መሰረት ቀደም ሲል ለኮርፖሬሽኑ ከተፈቀደው የእርሻ መሬት በተጨማሪ የኮርፖሬሽኑ እና የክልሉ የመሬት አስተዳደር ቢሮ ባለሞያዎች በጋራ ሆነው ጥናት በማካሄድ በአሶሳና ባምባሲ ዙሪያ ለበቆሎ ምርጥ ዘር ማባዣ ተስማሚ የሆነ የእርሻ መሬት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያፈላልጉ ገልጸዋል።
የተፈጥሮ ሙጫና እጣን ምርቶችን ለኮርፖሬሽኑ ከማቅረብ አኳያም፣ በማኅበር ከተደራጁ የክልሉ ወጣቶች ጋር በመነጋገር ምርቶቹን እንዲያቀርቡ እንደሚደረግ አስታውቀዋል። በሌላ በኩል የክልሉን ግብርና በመደገፍ ረገድ ኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎችን ለክልሉ አርሶና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ባለሃብቶች በማቅረብ፣ ሀገራዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
አክለውም ኮርፖሬሽኑ ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር በኮንትራት እርሻ በክልሉ እያካሄደ ከሚገኘው የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት በተጨማሪ የቅባት እህሎችን እንዲያመርት፣ የግብርና ግብዓቶችና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል እንዲያቋቁም፣ የዘር ብጠራ አገልግሎት እንዲሰጥ፣ የእርሻ መሣሪያዎች መለዋወጫዎች እንዲያቀርብ እና ከሽያጭ በኋላ የቴክኒክ ሞያ ሥልጠና እንዲያመቻች ጥሪ አቅርበዋል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በበኩላቸው፣ በቀጣይ የክልሉን የግብርና ልማት ይበልጥ ከማገዝ አኳያ የግብርና ግብዓቶችንና የእርሻ መሣሪያዎችን ከእነተቀጽላቸውና መለዋወጫቸው ጋር ለማቅረብ፣ ሁለገብ የግብርና ማዕከል ለማቋቋም፣ ለዜጓች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የዘር ብጠራ አገልግሎት እና የቴክኒክ ሞያ ሥልጠና ለመስጠት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።በተለይም የክልሉ ባለሃብቶች፣ አርሶና አርብቶ አደሮች ኮርፖሬሽኑ ለገበያ የሚያቀርባቸውን የእርሻ መሣሪያዎች በብድር ገዝተው እንዲጠቀሙ ለማገዝ ከክልሉ ጋር በመሆን የባንክ ብድር የማመቻቸት ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በመጨረሻም የክልሉ መንግሥት ለኮርፖሬሽኑ ልማት ውጤታማነት እያደረገ የሚገኘውን ሁለገብ ድጋፍ አድንቀው፣ ምስጋና አቅርበዋል።በውይይቱ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ኸሊፋ እና የርዕሰ መስተዳድሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ በቀለ አንበሳ እንዲሁም በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በኩል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ክፍሌ ወልደማርያም፣ የእርሻ መሣሪያዎችና የግብርና ውጤቶች አቅርቦት ዐቢይ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ፣ የደን ውጤቶች አቅርቦትና ሽያጭ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብዙነሽ ኢያሱ እና የአሶሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ድሪርሳ ተገኝተዋል።
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!



