* “ማዕከሉ የደበብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መሰረታዊ ችግር የነበረውን የግብርና ግብዓት አቅርቦት በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል” የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢንጂነር)
* “ማዕከሉ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አጎራባች ክልሎች እና ዞኖች ጭምር አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ነው።” የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1/2017 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በቦንጋ ከተማ ያስገነባው የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ተመረቀ።

የግብርና ሚኒስትር እና የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ “እንኳን ደስ አለን” ብለዋል። ማዕከሉ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አጎራባች ክልሎች እና ዞኖች ጭምር አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ መሆኑንም ገልጸዋል። ማዕከሉ በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ላለው ስኬት አንዱ ማሳያ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፣ የክልሉ አመራሮች ይህንን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም የአርሶ አደሮችን ሕይወት እንዲቀይሩ ጠቁመዋል።
“የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ የጀመርነው ጉዞ ውጤታማ ስለመሆኑ አንዱ ማረጋገጫ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት ነው፡፡” ያሉት ሚኒስትሩ፣ በተለይም ደግሞ ኩታ ገጠም ግብርናን በማስፋፋት እና የሜካናይዜሽን ተደራሽነትን በማሳደግ ሁሉንም የግብርና ወቅቶች በአግባቡ ለመጠቀም የተደረገው የተቀናጀ ጥረት በአርሶ አደሩ፣ ከፊል አርብቶ አደሩ እና በዘርፉ በተሰማሩ ባለሃብቶች ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትን ከመፍጠር ባለፈ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላለፉት የለውጥ ዓመታት በአማካይ ከ6 በመቶ በላይ ዓመታዊ እድገት እንዲያስመዘገብ አስችሏል ብለዋል፡፡ ለዚህ ስኬት ታሪካዊ አሻራቸውን ካኖሩ የልማት ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን መሆኑን አመልክተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው፣ ማዕከሉ የክልሉ መሠረታዊ ችግር የነበረውን የግብርና ግብዓት አቅርቦት በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል። ኮርፖሬሽኑ በሁሉም አካባቢዎች የልማት ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ እየሰራ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ በቦንጋ ከተማ የግብርና ግብዓት በስፋት የሚያቀርብ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያፋጥን ማዕከል በመገንባቱ የተቋሙን የሥራ አመራር ቦርድ እና የማኔጅመንት አባላት አመስግነዋል። የክልሉን የግብርና አቅም በአግባቡ ለመጠቀም የማዕከሉ መገንባት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመው፣ ማዕከሉ ያመጣቸውን በረከቶች በአግባቡ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል። በንግግራቸው ማጠቃለያም ኮርፖሬሽኑ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በቀጣይም ከኮርፖሬሽኑ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በበኩላቸው፣ ማዕከሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና አጎራባች አካባቢዎች የግብርና ግብዓቶችን፣ የእርሻ መሣሪያዎችን እና የሜካናይዜሽን አገልግሎትን በቅርበት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ በ743 ሚሊዮን ብር መገንባቱን አስታውቀዋል።
በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ለማዕከሉ ግንባታ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት የእውቅና የምስክር ወረቀት እና ዋንጫ ተሰጥቶአል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ሚኒስትሮች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የክልል እና ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮርፖሬሽኑ የቦርድ አባላት፣ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሥራ ኃላፊዎች፣ የቦንጋ እና ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የኮርፖሬሽኑ አመራሮች እና ሠራተኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!



















