
አዲስ አበባ፣ ጥር 28/2017 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት እውቅና አገኘ፡፡
በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም በተዘጋጀ የእውቅና መርሐ ግብር ላይ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ (ኢንጂነር) የእውቅና የምስክር ወረቀቱን ለኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም አስረክበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ጥራትን ማረጋገጥ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን አስገንዝበው፣ ኮርፖሬሽኑ ይህንን ተረድቶ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን በመዘርጋቱ በዛሬው ዕለት እውቅና ለማግኘት ችሏል ብለዋል፡፡ እውቅናውን ለማስቀጠል ከአመራሩና ሠራተኛው ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግም አክለው ጠቁመዋል፡፡ በመልእክታቸው ማጠቃለያም ሌሎች ተቋማት ከኮርፖሬሽኑ ትምህርት በመውሰድ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን እንዲተገብሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር እና የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባል ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ ኮርፖሬሽኑ መንግሥት ለጥራት የሰጠውን ትኩረት ተረድቶ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን የጥራት አመራር ሥርዓት በመተግበር እውቅና በማግኘቱ የተቋሙን የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች አመስግነው፣ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የተሰማራበት የግብርና ዘርፍ የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ምርት በጥራት እንዲመረት እና ምርታማነት እንዲያድግ ተቋሙ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ትግበራን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ (ዶ/ር) በዕለቱ ባስተላለፉት መልእክት፣ ኮርፖሬሽኑ በጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት በራሱ ተነሳሽነትና ትጋት እውቅና ማግኘቱን ጠቁመው፣ ይህ ቀን የድል ብቻ ሳይሆን የአሠራር ሥርዓቱን በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠል ቃል የሚገባበት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፣ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት እውቅና ማግኘት በኮርፖሬሽኑ የዘጠኝ ዓመት የልማት ጉዞ ከተመዘገቡ ስኬቶች አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ እውቅናው ለኮርፖሬሽኑ ቀጣይ እድገት መሰረት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው በንግግራቸው ማጠቃለያ፣ ኮርፖሬሽኑ በጥራት ሥራ አመራር እውቅና እንዲያገኝ አስተዋጽዖ ለነበራቸው አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ያገኘው እውቅና ለሦስት ዓመታት የሚያገለግል ነው፡፡
የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ትግበራን በማስቀጠል ግብርናን የማዘመን ግባችንን እናሳካለን!





























