* “ኮርፖሬሽኑ ክልሉን ለመደገፍ ቀድሞ የተገኘ ተቋም በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል” የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ኃላፊ
አክሱም፣ ታህሳስ 11/2017 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን በጦርነት ፈርሰው የነበሩ የውቅሮ ማራይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የመማሪያ ክፍሎችን በ7.5 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ አስገንብቶ እና የውስጥ ቁሳቁስ አሟልቶ ታህሳስ 11 ቀን 2017 ዓ.ም አስመረቀ።
በምረቃ እና ርክክብ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ኪሮስ ጉዑሽ (ዶ/ር) በአስተላለፉት መልእክት፣ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የትግራይ ክልልን ለመደገፍ ከሀገር ውስጥ ተቋማት ቀድሞ የተገኘ ድርጅት ነው ብለዋል።
ለዚህም በትግራይ ሕፃናት፣ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ሕዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።በመልእክታቸው ማጠቃለያም፣ ሌሎች የልማት ድርጅቶች ኮርፖሬሽኑ የፈጸመውን በጎ ተግባር በአርአያነት ወስደው ክልሉን በትምህርት እና በተለያዩ መስኮች እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
በተመሳሳይ የክልሉ የማዕከላዊ ዞን የታህታይ ማይጨው ወረዳ የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ መምህር ጎይቶም በየነ፣ ኮርፖሬሽኑ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለመገንባት የአደረገውን ጥረት አድንቀው፣ በውቅሮ ማራይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች እና በወረዳው ስም አመስግነዋል።
ተማሪዎች እና የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ በጦርነት የፈረሱ የመማሪያ ክፍሎችን መልሶ በመገንባት እንዲሁም ጠረጴዛ እና ሰሌዳ በማሟላት ክፍሎቹን ማስረከብ በመቻሉ እመስግነዋል። በቀጣይም የኮርፖሬሽኑ ተጨማሪ ድጋፍ እንደማይለያቸው አስታውቀዋል።
በዕለቱ መርሐ ግብር ላይ ንግግር የአደረጉት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም እንደገለጹት፣ የኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር “የተማረ ዜጋ መፍለቂያ ትምህርት ቤት መገንባት፣ ማኅበራዊ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው” በሚል እሳቤ በሰጠው ውሳኔ መሰረት 7.5 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ካፒታል በጦርነት ፈርሰው የነበሩ የመማሪያ ክፍሎች መልሰው እንዲገነቡ እና የውስጥ ቁሳቁስ እንዲሟላላቸው በማድረግ አገልግሎት ማስጀመር ተችሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ኮርፖሬሽኑ በ305 ሺህ ብር ያሳተማቸውን 2 ሺህ የመማሪያ ደብተሮች በ2016 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ለታህታይ ማይጨው ወረዳ በድጋፍ መልክ ማስረከቡን አስታውሰዋል፡፡በቀጣይም የኮርፖሬሽኑ የፋይናንስ አቅም እየታየ ተጨማሪ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል፡፡
በመጨረሻም የማዕከላዊ ዞን የታህታይ ማይጨው ወረዳ የትምህርት ጽ/ቤት የአዘጋጀውን ሥጦታ ለአቶ ክፍሌ ወልደማርያም፣ ለዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ እና ለአቶ ኪያ ተካልኝ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ተወካይ አበርክቷል።
የውቅሮ ማራይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከአክሱም ከተማ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ###
ግብርናን ከማዘመን ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን በመወጣት ለሕዝብ ያለንን አጋርነት እናረጋግጣለን!