“ኮርፖሬሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በአከናወነው የግብርና ልማት እውቅና እያገኘ ነው” የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር
አዲስ አበባ፣ ህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በአጭር ጊዜ ውስጥ በአከናወነው የግብርና ልማት ሥራዎች እውቅና እያገኘ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ገለጹ፡፡ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ማስረሻ በላቸው ይህንን የገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ በክልሉ እያደረገ ያለውን የግብርና ልማት እንቅስቃሴ በማስመልከት ከተቋሙ የኮሚዩኒኬሽን ቡድን ጋር በአደረጉት ቃለ መጠይቅ ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከክልሉ አርሶ አደሮች እና በግብርና ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር በቀላሉ በመተዋወቅ እና በመተባበር በጋራ እየሰራ መሆኑን የአስረዱት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ከዚህ የተነሳ በአጭር ጊዜ ውስጥ በክልሉ እውቅና ማግኘት፣ ስሙን መትከል እና በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል ብለዋል፡፡አክለውም ኮርፖሬሽኑ በኮንትራት እርሻ አብሮአቸው ከሚሰራው አርሶ አደሮች ጋር ጠንካራ የሥራ ግንኙነት ከመፍጠር ባሻገር፣ ለአርሶ አደሮቹ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ ግብዓት በማቅረብ እና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ለአካባቢው አዲስ ልምድ የሆኑትን በትራክተር የማረስ እና ምርትን በአጭዶ መውቂያ (ኮምባይን ሀርቨስተር) የመሰብሰብ ዘመናዊ የግብርና ተሞክሮዎችን የአስተዋወቀ እና የአለማመደ ድርጅት ነው ያሉት አቶ ማስረሻ፣ ተቋሙ ወደ ቦንጋ ከመምጣቱ በፊት የሜካናይዜሽን አገልግሎት በክልሉ የተለመደ እንዳልነበር አስታውሰዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የሀገሪቷን ግብርና ለማዘመን ከያዘው ግብ አኳያ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን በአካባቢው በማስተዋወቁ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና ባለሃብቱ ምርታቸው በአጭዶ መውቂያ (ኮምባይን ሀርቨስተር) እንዲሰባሰብላቸው ለኮርፖሬሽኑ ጥያቄ ማቅረባቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የሚጀምረውን የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓት እና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ ማዕከሉ የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም፣ ግብርናን በማዘመን እና ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ የግብርና እመርታ ለማስመዝገብ እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡ማዕከሉ ከክልሉ አልፎ አጎራባች ዞኖችና ክልሎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል አቅም ያለው መሆኑንም አቶ ማስረሻ አመልክተዋል፡፡ከዚህ ባሻገር ኮርፖሬሽኑ ታማሻሎ ተብሎ በሚጠራ የክልሉ አካባቢ ምርጥ ዘር እያባዛ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ዘሮችን በማባዛት፣ በቦንጋ ማዕከል በማበጠር እና በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች እና ለባለሃብቶች ምርጥ ዘር በማቅረብ የክልሉን እና የአጎራባቾችን የዘር ችግር እንደሚቀርፍ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም የቦንጋ ማዕከል በክልሉ በግብርና ልማት መስክ ላይ ለተሰማሩ አካላት የእርሻ መሣሪያዎችን በሽያጭና በኪራይ በማቅረብ እንዲሁም የምክር፣ የጥገና እና የቴክኒክ ሞያ የሥልጠና አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ለክልሉ የግብርና ዘርፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡
በኮርፖሬሽኑ ላይ ያላቸው ተስፋ ከፍተኛ መሆኑን የአስታወቁት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ተቋሙ የጀመረውን የልማት ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና በእንስሳት ልማት በኩል የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለክልሉ እንዲያቀርብ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በጨረሻም ከኮርፖሬሽኑ ብዙ ተምረናል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ተቋሙን በቅርበት በመደገፍ የተጀመረውን የሥራ ግንኙነት አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ አስታውቀዋል።
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!