አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና በተቋሙ መሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር መካከል ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም 4ኛው የኅብረት ስምምነት ተፈረመ።
በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በአስተላለፉት መልእክት፣ ለቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚቆየው ይህ የኅብረት ስምምነት ሁለቱ ተደራዳሪ አካላት ተቀራርበው በመስራታቸው ለውጤት በቅቷል ብለዋል።
የስምምነቱ ዓላማ የሠራተኛውን የሥራ ዋስትና፣ ምርትና ምርታማነትን እንዲሁም የኢንደስትሪ ሰላምን ማረጋገጥ መሆኑን የገለጹት አቶ ክፍሌ፣ ለስምምነቱ መሳካት አስተዋጽዖ ያደረጉ የሥራ አመራር እና የሠራተኛ ማኅበር ተደራዳሪዎችን አመስግነዋል።
አያይዘውም መሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበሩ ለኮርፖሬሽኑ ቀጣይ እድገት እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በላቀ የሥራ ተነሳሽነት፣ ቁርጠኝነት እና ተግባቦት ለበለጠ ስኬት እንደሚሰራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የኮርፖሬሽኑ የመሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ ደበሌ በበኩላቸው፣ በኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር እና በማኅበሩ መካከል የተደረሰው የኅብረት ስምምነት የሠራተኞች መብቶች፣ ጥቅሞች እና ግዴታዎች የሚረጋገጡበት ነው ብለዋል።
እክለውም ስምምነቱ በሥራ አመራሩ እና በማኅበሩ መካከል ከዚህ ቀደም የተፈጠረውን ጠንካራ የሥራ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና በተቋሙ መሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር መካከል ላለፉት ወራት ሲደረግ የቆየው 4ኛው የኅብረት ስምምነት ድርድር ሂደትን አስመልክተው የኮርፖሬት ሀብት አመራር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተንሳይ ሜጫ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም የኅብረት ስምምነት ድርድር ሰነድ ርክክብ ተደርጓል።
###
አንድነታችንን በማስቀጠል ግብርናን የማዘመን ግባችንን እናሳካለን!