አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2016 በጀት ዓመት 1 ሺህ 450 ኩንታል የእጣን፣ ሙጫ፣ ከርቤ እና አበከድ የደን ውጤቶችን ወደተለያዩ የዓለም ሀገራት በመላክ 846 ሺህ የአሜሪካ ዶላር አገኘ፡፡በተጨማሪም ለሀገር ውስጥ ገበያ 1 ሺህ 498 ኩንታል የእጣን፣ ሙጫ፣ ከርቤ እና አበከድ ምርቶችን በማቅረብ 13 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘት ችሏል፡፡በኮርፖሬሽኑ የአዳማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳለ ታደሰ እጣን፣ ሙጫ፣ ከርቤ እና አበከድ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ገበያዎች ተፈላጊ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ እነዚህን የደን ውጤቶች ከሀገሪቷ ቆላማ አካባቢዎች በማምረትና በግዥ እንደሚሰበስብ የጠቆሙት አቶ እንዳለ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰበሰበውን እጣንና ሙጫ አዳማ በሚገኘው ማዕከል በማበጠር፣ ደቃቁንና አንኳሩን በመለየት፣ በቀለምና በመጠን ደረጃ በማውጣት፣ በማሸግ እና በማዘጋጀት ወደ ውጭ እንደሚልኩ አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 4 ሺህ ኩንታል የደን ውጤቶች በክምችት እንደሚገኙ እና ወደ ውጭ ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከሚሰበስበው እጣን ውስጥ አብዛኛው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሲሆን፣ ለመድኃኒት፣ ለጨርቃጨርቅ፣ ለመጠጥ፣ ለኮስሞቲክስ ወዘተ ማምረቻ ፋብሪካዎች በግብዓትነት ይውላል።
በሌላ በኩል ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበው እጣን በአብዛኛው በቤት ውስጥ እና በተለያዩ ቦታዎች የሚጨስ መሆኑን አቶ እንዳለ አክለው ገልጸዋል፡፡