ለ2017/18 የምርት ዘመን 25 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ይፈጸማል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26/2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2017/18 የምርት ዘመን ለመስኖ እርሻ የሚውል ዳፕ እና ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ለማጓጓዝ የግዥ ሂደት ጀመረ። በምርት ዘመኑ 25 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ይፈጸማል።
የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ መሰረት ለመስኖ እርሻ የሚውል ዳፕ እና ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለማቅረብ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
ለ25 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ (13 ሚሊየን ኩንታል ዩሪያ እና 12 ሚሊየን ኩንታል ዳፕ) ግዥ 1.3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በመንግሥት ተፈቅዷል።
ለ2016/17 የምርት ዘመን በ930 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ከውጭ ከተገዛው 20 ሚሊየን ኩንታል ያህል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስከአሁን ከ18.8 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ በመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሮች እየቀረበ ነው።
መንግሥት በአፈር ማዳበሪያ ግዥ ላይ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ አዲስ የግዥ መመሪያ በማውጣቱ ከግዥ ጋር የተያያዙ ችግሮች ተፈተዋል። በዚህም ማዳበሪያን ቀደም ብሎ መግዛት እና ማጓጓዝ በመቻሉ ባለፈው የምርት ዘመን 21 ቢሊየን ብር ለማዳን ተችሏል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር በየዓመቱ እያጠና በሚያቀርበው የሀገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት መሰረት የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ዓለም አቀፍ ጨረታ እያወጣ የማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም ላይ ይገኛል።
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!