“ተቋሙ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ በመሆኑ ቦርዱ የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደርጋል” የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2016 በጀት ዓመት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) የተቋሙን የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህን የገለጹት፣ የ2016 ዓ.ም የሠራተኞች ዓመታዊ የማጠቃለያ ስብሰባ እና የ2017 አዲስ ዓመት ዋዜማ ልዩ የመዝናኛ መርሐ ግብር ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተቋሙ ላስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት የኮርፖሬሽኑን ሥራ አመራር ቦርድ፣ ማኔጅመንቱን እና ሠራተኞችን አመስግነዋል፡፡የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ለኮርፖሬሽኑ የልማት ሥራዎች አስፈላጊውን የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ እና በሽርክና ከውጭ ኩባንያዎች ጋር የሚሰራበትን ሁኔታዎች እንደሚያመቻች ዋና ሥራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል፡፡ኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽን ሥራዎችን እንዲያስፋፋ እና እንዲያጠናክር፣ ለገበያ የሚያቀርባቸውን ምርቶች እና አገልግሎቶች በአይነት፣ በጥራትና በመጠን እንዲያሳድግ እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የንግድ ፖርትፎሊዮ ዳይሬክተር አቶ ኪያ ተካልኝ በበኩላቸው፣ ከማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ኮርፖሬሽኑ የሥራ ማስኬጃ እጥረት እንዳያጋጥመው ካፒታሉን ለማሳደግ ተቋማቸው ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ወልደአብ ደምሴ በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ በግብርናው መስክ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ በመሆኑ ቦርዱ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፣ ኮርፖሬሽኑ ላለፉት ዓመታት በርካታ ስኬቶችን እንዲያስመዘግብ ስትራቴጂካዊ አመራር የሰጠውን የሥራ አመራር ቦርድ፣ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ያደረገውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፣ ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ ያደረጉትን የኮርፖሬሽኑ የሥራ መሪዎች እና ሠራተኞች እንዲሁም በተቋሙ ስኬት ላይ አስተዋጽዖ የነበራቸውን የባለድርሻ አካላት አመስግነዋል፡፡የኮርፖሬሽኑ የመሰረታዊ ሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ ደበሌ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት፣ ሠራተኞች አንድነታቸውን ጠብቀው በየተሰማሩበት የሥራ መስክ የተጣለባቸውን አደራ እንዲወጡ አሳስበው፣ ለጋራ ስኬት በቁርጠኝነት እንስራ ብለዋል።
በዕለቱ የኮርፖሬሽኑ የስፖርት ማዕከል (ጂምናዚየም) በተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ተመርቋል፡፡
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!