* “የዛሬው ዕለት ለኮርፖሬሽኑ ታሪካዊ ቀን ነው” የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ
* “የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት የጀርባ አጥንት ለሆነ ተቋም የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት እንዲተገብር የማማከር እና የመደገፍ ሥራ እያከናወንን በመሆኑ ታላቅ ደስታ እና ኩራት ይሰማናል” የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት የሙከራ ትግበራ ጀመረ፡፡
በኮርፖሬሽኑ የስብሰባ አዳራሽ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት የሙከራ ትግበራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም እንደተናገሩት፣ ዕለቱ ኮርፖሬሽኑ የISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን በመተግበር ከዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል አንዱ የሚያደርገው ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል፡፡አክለውም ሁሉም የሥራ መሪዎች እና ሠራተኞች የአሠራር ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን በቁርጠኝነት በመስራት አሻራቸውን እንዲያኖሩ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡አያይዘውም የአሠራር ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ በተከናወኑ ሥራዎች ላይ አስተዋጽዖ ለአበረከቱ በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በሙከራ ትግበራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ “የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት የጀርባ አጥንት ለሆነ ተቋም የISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት እንዲተገብር የማማከር እና የመደገፍ ሥራ እያከናወንን በመሆኑ ታላቅ ደስታ እና ኩራት ይሰማናል” በማለት ተናግረዋል፡፡አክለውም ኮርፖሬሽኑ የሰነድ ሥራዎችን እና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችን በአጭር ጊዜ አከናውኖ ወደ ሙከራ ትግበራ መግባቱ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው፣ የተቋሙን ሥራ አመራር እና ሠራተኞች እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡ ISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን ለመተግበር ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በዚህ ረገድ የኮርፖሬሽኑ አመራሮች እና ሠራተኞች ያላቸው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን መተግበር በትርፋማነት እና አሠራር ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ተቋማቸው ኮርፖሬሽኑ የአሠራር ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ እንዲተገብር በተለየ ሁኔታ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ የሙከራ ትግበራ ሥራው እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፣ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ እና ቁርጠኛ መሆናቸውን በሰጡት አስተያየት አስታውቀዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዕለቱ መርሐ ግብር የISO ዶክመንት ርክክብ የተደረገ ሲሆን፣ ሰነዶቹን ለአራት የዘርፍ ኃላፊዎች የአስረከቡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ከኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት እና ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ተውጣተው የISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት የአተገባበር ሥልጠና የወሰዱ 39 ሠራተኞች ከኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ (ዶ/ር) እጅ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡
###
የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን በመተግበር ግብርናን የማዘመን ግባችንን እናሳካለን!