ሮቤ፣ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በባሌ ሮቤ ከተማ 1 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ ያስገነባው የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተመርቆ የቁልፍ ርክክብ ተፈጽሟል።
ኮርፖሬሽኑ መኖሪያ ቤቱን ያስገነባው በሮቤ ከተማ በሃቢፍቱ ቀበሌ ነዋሪ ለሆኑት ወይዘሮ መክዳ አብዱራሂም ነው።
በምረቃ እና በቁልፍ ርክክብ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በአደረጉት ንግግር፣ ኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ተቋም እንደመሆኑ ለሕዝብ ያለውን አጋርነት ለማረጋገጥ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።
በዕለቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከሮቤ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን መኖሪያ ቤቱን መርቀው ለወይዘሮ መክዳ አብዱራሂም ቁልፍ አስረክበዋቸዋል። ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ዓመታት ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር እና ከሚያገኘው ትርፍ ላይ በየዓመቱ ለማኅበራዊ ኃላፊነት በጀት በመመደብ በተለያዩ አካባቢዎች ለበርካታ ማኅበረሰቦች የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አቶ ክፍሌ አብራርተዋል፡፡
አክለውም ኮርፖሬሽኑ በ2016 በጀት ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ከማስቀጠል ባሻገር ለተለያዩ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ከ16 ሚሊየን ብር በላይ ማውጣቱን ጠቁመው፣ ኮርፖሬሽኑ ከአከናወናቸው ሥራዎች አንዱ የወይዘሮ መክዳ አብዱራሂም መኖሪያ ቤት ግንባታ መሆኑን አስታውቀዋል።
በቀጣይም የኮርፖሬሽኑ የፋይናንስ አቅም እየታየ ተጨማሪ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል። በኮርፖሬሽኑ የውስጥ አቅም በ885 ሺህ 197 ብር ወጪ በ63 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባው የወይዘሮ መክዳ መኖሪያ ቤት በብሎኬት የተሰራ ሲሆን፣ ከተገነባ 48 ዓመታት ሞልቶት የነበረውን የቀድሞውን አሮጌ ቤት አፍርሶ ለመገንባት 55 ቀናት ወስዷል፡፡ በአዲስ መልክ የተገነባው ይህ መኖሪያ ቤት ሳሎን እና ሁለት የመኝታ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስም ተሟልቶለታል፡፡ በሀገር ሽማግሌዎች እና በአባ ገዳዎች ምርቃት የተጀመረው የዕለቱ የምረቃ እና የቁልፍ ርክክብ ሥነ ሥርዓት የሮቤ ከተማ አስተዳደር የበሃቢፍቱ ቀበሌ መስተዳድር ለኮርፖሬሽኑ የበላይ አመራሮች የጋቢ ሥጦታ አበርክቶ ተጠናቋል። በተመሳሳይ ዜና ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ያስገነባውን ተጨማሪ የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚያስመርቅ ይጠበቃል። ግብርናን ከማዘመን ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን በመወጣት ለሕዝብ ያለንን አጋርነት እናረጋግጣለን!