የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን Ethiopian Agricultural Businesses Corporation

ኮርፖሬሽኑ ከአውሮፓ ከሚያስመጣቸው 75 ትራክተሮች ውስጥ 59ኙን ተረከበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም. (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአውሮፓ ከሚያስመጣቸው 75 ትራክተሮች ውስጥ 59ኙን ተረከበ።

በኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት፣ ማርኬቲንግና ሽያጭ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎሳዬ ቶሎሳ እንዳስታወቁት፣ ኮርፖሬሽኑ የሀገሪቷን ግብርና ለማዘመን የሚያስችሉ የእርሻ መሣሪያዎችን ከእነተቀጽላቸው ከአውሮፓ እና ከቻይና እያስመጣ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከ110 እስከ136 የፈረስ ጉልበት ያላቸውን  ‘ዜቶር’ በመባል የሚታወቁ ትራክተሮችን ከቼክ ሪፐብሊክ እያስመጣ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ከታዘዙ 75 ትራክተሮች ውስጥ እስከአሁን 59ኙን መረከባቸውን አስታውቀዋል፡፡ ቀሪዎቹ 16 ትራክተሮችም በቅርቡ  ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

ዜቶር ትራክተር ላይ የቴክኒክ ብልሽት ቢያጋጥም መለስተኛ የእጅ መሣሪያዎችን በመጠቀም በቀላሉ መጠገንና ማስተካከል እንደሚቻልም አስረድተዋል። ኮርፖሬሽኑ ትራክተሮችን ከማቅረብ ባሻገር ከሽያጭ በኋላ ለደንበኞች የቴክኒክና ሞያ ሥልጠና፣ የጥገና እና የምክር አገልግሎቶች አዲስ አበባ በሚገኘው የቴክኒክና ሞያ ማሠልጠኛ ማዕከል እና በቅርንጫፎቹ እየሰጠ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የአርሶ አደሮች እና የባለሀብቶች ሰብል እየሰበሰበ ነው

ለመተሃራ ስኳር ፋብሪካ 700 ሄክታር የሸንኮራ አገዳ ማሳ እያዘጋጀ ይገኛል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም. (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአርሶ አደሮችን፣ በግብርና ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶችን እና የተለያዩ ድርጅቶችን የደረሰ ሰብል በተመጣጣኝ ዋጋ እየሰበሰበ ነው፡፡በኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎች እና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ክፍሌ እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ ከጥቅምት 2016 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በሞጆ እና ሄረሮ ዙሪያ ለሚገኙ አርሶ አደሮች እና ባለሀብቶች የሰብል መሰብሰብ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡የሀገሪቱ የግብርና ምርት ሙሉ በሙሉ እስኪሰበሰብ ድረስ ኮርፖሬሽኑ አገልግሎቱን እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ መንግሥቱ፣ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ በጎጃም የአየሁ እርሻ ልማት የደረሰ ሰብል እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል፡፡እንደ ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ፣ ኮርፖሬሽኑ በ10 አጭዶ መውቂያ መሣሪያዎች የሰብል መሰብሰብ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ አገልግሎቱን ለማጠናከር ተጨማሪ 10 አጭዶ መውቂያዎችን ከውጭ አስመጥቶአል።

አቶ መንግሥቱ ክፍሌ

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ የመተሃራ ስኳር ፋብሪካን ነባር የሸንኮራ አገዳ በማስወገድ ለአዲስ የሸንኮራ አገዳ ተከላ 700 ሄክታር መሬት እያዘጋጀ መሆኑን አቶ መንግሥቱ አክለው አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በክልሎች ካሉት 25 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ውስጥ የሞጆ፣ ሄረሮ እና ቡሬ ጣቢያዎች በዋናነት የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ለማስፋፋት እና ለማጠናከር የተቋቋሙ ናቸው፡፡

ኮርፖሬሽኑ በትራክተር የሚጎተቱ ጣልያን ሰራሽ የኬሚካል መርጫ ማሽኖችን አስመጣ

ከቻይናው ዙምላይን የገዛቸው ኮምባይን ሀርቨስተሮችም ጂቡቲ ወደብ ደርሰዋል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ):-የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) በትራክተር የሚጎተቱ 15 ጣልያን ሰራሽ የኬሚካል መርጫ ማሽኖችን በ425 ሺህ 280 የአሜሪካን ዶላር (23 ሚሊዮን 605 ሺህ 251.456 ብር) አስመጣ።
በእርሻ መሣሪያዎች እና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት፣ ማርኬቲንግና ሽያጭ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎሳዬ ቶሎሳ እንዳስታወቁት፣ እያንዳንዱ ማሽን 3 ሺህ ሊትር አግሮኬሚካሎችን የመያዝ አቅም አለው።አክለውም ማሽኖቹ 24 ሜትር ስፋት እና ቁመታቸውም እስከ 2 ሜትር ከፍ እንደሚል ገልጸዋል።በሌላ ዜና ኮርፖሬሽኑ ከቻይናው ዙምላይን የእርሻ መሣርያ አምራች ኩባንያ ጋር ሰኔ 25/2015 ዓ.ም በገባው የንግድ ስምምነት መሰረት የገዛቸው 10 ኮምባይን ሀርቨስተሮች ጂቡቲ ወደብ መድረሳቸውን አቶ ጎሳ ተናግረዋል።ኮምባይን ሀርቨስተሮቹ በ648 ሺህ 600 የአሜሪካን ዶላር (36 ሚሊዮን 672 ሺህ 72 ብር) መገዛታቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዘው ለ2015/16 የምርት ዘመን የአጨዳ ሥራ እንደሚደርሱ አስታውቀዋል።