የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን Ethiopian Agricultural Businesses Corporation

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአቢሲኒያ የጥራት ሽልማት ድርጅት የተዘጋጀውን የመጀመሪያ የኢንደስትሪ ሽልማት አገኘ።

በኢንተርሌግዠሪ ሆቴል መጋቢት 24/2015 ዓ.ም. በተዘጋጀ የኢንደስትሪ ሽልማት መርሐ ግብር ላይ ኮርፖሬሽኑ የወርቅ ዋንጫ፣ የወርቅ ሜዳሊያ እና ከፍተኛ የክብር ዲፕሎማ አግኝቷል። ሽልማቱን ከዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እጅ የተቀበሉት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ናቸው።

በተመሳሳይ  የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በግላቸው የሥራ አመራር ከፍተኛ የክብር ኮርደን/GOLD Honor CORD ሽልማት እና በኢንደስትሪ ሥራ አመራር የላቀ አፈጻጸም የክብር ዲፕሎማ (Diploma of the Legion of Honour) ከቀድሞ ፕሬዝዳንት እጅ ተቀብለዋል። እንዲሁም የኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽን ዐቢይ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ ከቀድሞ ፕሬዝዳንት እጅ  የወርቅ ኒሻንና የትጉህ አመራር የክብር ዲፕሎማ ተሸልመዋል። በተጨማሪም ሦስት አመራሮችና ዘጠኝ ሠራተኞች የወርቅ ሜዳሊያና የትጉህ ሠራተኝነት የክብር ዲፕሎማ ከአቢሲኒያ የጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አሰፋ ከሲቶ እጅ ተቀብለዋል።

በሽልማት መርሐ ግብሩ ላይ የዕለቱን የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የኢንደስትሪ ተቋማት አመራሮች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ተሽላሚዎችና ቤተሰቦቻቸው ተገኝተዋል። በኮርፖሬሽኑ በኩል በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ወልደአብ ደምሴ፣ በሠራተኛ የተመረጡ የቦርድ አባላት፣ የመሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ሓላፊዎች፣ የማኔጅመንት አባላት እና ሠራተኞች ተገኝተዋል።

“ዓለምንና ሕዝቦቿን የሚታደግ የላቀ ሥራ ለሰሩ ትጉሃን እንሸልማለን!” የሚል መሪ ቃልን አንግቦ በተለያዩ የሞያ መስኮች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችን በየዓመቱ በመሸለም የሚታወቀው “አቢሲኒያ ዓለም አቀፍ ሽልማት ድርጅት” ከ2010 እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ ባደረገው ጥናት ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢንደስትሪ ሽልማት ካጫቸው ከ57 ሺህ በላይ አምራች እና አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት፣ የግል እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ 50 ተሸላሚዎችን የመረጠ ሲሆን፣  የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) አንዱ በመሆን ተሸልሟል።

በአቢሲኒያ የጥራት ሽልማት ድርጅት የተሸለሙ የኢግሥኮ ትጉሃን የሥራ አመራሮችና ሠራተኞች ስም ዝርዝር

1.
 አቶ ክፍሌ ወልደማርያም
2. አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ
3. አቶ ዘነበ ወልደሥላሴ
4. አቶ ሰለሞን ገብሬ
5. ወይዘሮ መንበረ ኃይለማርያም
6. ወይዘሮ አመለወርቅ ዓለምአየሁ – ከግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ
7. ወይዘሮ ነፃነት ረቡማ – ከግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ
8. አቶ ተስፋሁን አበበ አንጀሎ – ከእርሻ መሣሪያዎችና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ
9. አቶ ሲራክ ደገፋ – ከእርሻ መሣሪያዎችና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ
10. አቶ ሲዳ ለታ – ከኢትዮጵያ ምርጥ ዘር እና ደን ውጤቶች ዘርፍ
11. አቶ ሻምበል ገላን – ከኢትዮጵያ ምርጥ ዘር እና ደን ውጤቶች ዘርፍ
12. አቶ ግርማ ፋሪስ – ከተሽከርካሪዎች አስተዳደርና ጥገና ዘርፍ
13. አቶ ተከስተ ተክሌ – ከተሽከርካሪዎች አስተዳደርና ጥገና ዘርፍ
14. አቶ ዳንኤል ስንሻው – ከዋናው መ/ቤት

አቢሲኒያ የጥራት ሽልማት አሰጣጥ መርሐ ግብር 

በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከ117 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር መሰብሰቡን አስታወቀ

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቡሹራ መሐመድ እንዳስታወቁት፣ ጽ/ቤቱ በ2014/15 የምርት ዘመን በባሌ እና አርሲ ዞኖች ከባለሀብቶች እና የግብርና ኮሌጆች በኮንትራት ማዕቀፍ 120 ሺህ ኩንታል ዘር ለማምረት አቅዶ፣ ከ117 ሺህ ኩንታል በላይ ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

ይህም የእቅዱን 97.5 ከመቶ ነው ያሉት አቶ ቡሹራ፣ የተሰበሰበው ምርት በጽ/ቤቱ ታሪክ ከፍተኛው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከተሰበሰበው ዘር ውስጥም ከ10 በላይ የስንዴ እና ገብስ ዝርያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተሰበሰበውን ዘር ኮፈሌ ከተማ በሚገኘው የማበጠሪያ ማሽን በማበጠርና በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ እስከ መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር አበጥረው ማዘጋጀታቸውን እና ቀሪው በአጭር ጊዜ ተዘጋጅቶ ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጭ አብራርተዋል፡፡  አቶ ቡሹራ በቀጣይም የምርጥ ዘር አቅርቦትን ለማሳደግ ሌሎች ተጨማሪ ባለሀብቶች ከኮርፖሬሽኑ ጋር በጋራ ዘር እንዲያባዙ  ለማድረግ ማነጋገራቸውንና ከባለሀብቶቹም አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2014/15 የምርት ዘመን ከኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መካከል በምርጥ ዘር ብዜት ከፍተኛ ምርት በመሰብሰብ ቀዳሚ ሲሆን፣ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ደረጃ 117 ሺህ ኩንታል ምርት ሲሰበሰብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ደረጃ እስከ አሁን ከተሰበሰበው ከ265 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ውስጥ 105 ሺህ 173 ኩንታል ተበጥሮ ተዘጋጅቷል።

                         ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመንግሥት ከተሰጠው ሰፊ ተልዕኮ አንጻር የበርካታ ቋሚ ኮሚቴዎች ድጋፍ እንደሚያስፈልገው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገለጹ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ዶክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዶ ይህንን የገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዳማና በአዲስ አበባ ከተሞች ከመጋቢት 8-9/2015 ዓ.ም. ድረስ ባዘጋጀው የውይይትና የጉብኝት መርሐ ግብር ማጠቃለያ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ ግብርናን ለማዘመን እያከናወናቸው ለሚገኘው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር የኮርፖሬሽኑ ሥራዎች የሚመለከታቸው ሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች ተቋሙን ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው ፕሮፌሰር መሐመድ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አኳያም የኮርፖሬሽኑን ልማት ለመደገፍና ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የሚገኙበት የጋራ የውይይት መድረክ እንደሚዘጋጅ አስታውቀዋል፡፡ በአዳማ ሂል ሳይድ ሆቴል የተካሄደውን የውይይት መድረክ የመሩት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ በተደረገላቸው ገለጻ ኮርፖሬሽኑ በግብርናው ዘርፍ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገንዝበዋል፡፡

አክለውም ኮርፖሬሽኑ ሲቋቋም የተፈቀደለትን ካፒታል በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማሟላት መቻሉን እና በየዓመቱ እያተረፈ የሚሄድ ተቋም መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ ለሀገሪቷ የምጣኔ ሀብት እድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽዖ እና ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የሚያከናውናቸው የድጋፍ ሥራዎች አበረታች ናቸው ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፣ በቀጣይ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡ኮርፖሬሽኑ በበርካታ የሥራ መስኮች አፈጻጸም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፣ የመስኖ ልማት እና የእርሻ መሬት በማስፋፋት ወደ ውጭ የሚላኩ ሰብሎችን ለማምረት የጀመረውን እንቅስቃሴ አበረታተዋል፡፡ በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ለኮርፖሬሽኑ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀው፣ ከምርምር ተቋማትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር የሚያደርገውን ግንኘነት አጠናክሮ እንዲቀጥል አስተያየት ሰጥተዋል፡ከተደረገላቸው ገለጻና በአካል ከተመለከቷቸው የሥራ እንቅስቃሴዎች በመነሳት “ኮርፖሬሽኑ ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር የሚገባውን ያህል ትኩረት አላገኘም” ያሉት የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያን አርሶ አደር አቅፎ የያዘ ተቋም መሆኑን ተረድተናል ብለዋል፡፡አያይዘውም የተቋሙ ስትራተጂክ ዕቅድ ከሀገሪቷ የ10 ዓመት የግብርና ዘርፍ መሪ ዕቅድ ጋር ተጣጥሞ መዘጋጀቱ ለቀጣይ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለተግባራዊነቱም ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የደን ውጤቶችን (ሙጫ፣ እጣን፣ ከርቤና አበክድ) ለመሰብሰብና ወደ ውጭ ለመላክ የሚደረገው እንቅስቃሴ መጠናከር እንዳለበት፤ የግብርና ግብዓት አቅርቦትን ማስፋት እንደሚገባ፤ የማዳበሪያ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ ማቋቋም እንደሚያስፈልግ፤ ለኦርጋኒክ ማዳበሪያ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት እንዲሁም የእርሻና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች የቴክኒክ ማሠልጠኛ ማዕከልን በአዳዲስ የሥልጠና ማቴሪያሎች ማጠናከር እንደሚገባ የጠቆሙት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣  ኮርፖሬሽኑ ግብርናን ለማዘመን ያከናወናቸውን ሥራዎች በማድነቅ የተቋሙን የሥራ ኃላፊዎች አበረታተዋል፡፡የኮርፖሬሽኑን አጠቃላይ ገጽታ እና የልማት ሥራዎች ለቋሚ ኮሚቴው ገለጻ ያደረጉት የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም፣ በተለይም ከካፒታል ማሳደግ፣ ከአፈር ማዳበሪያ ግዥ ሥርዓት ደንብ ማውጣት፣ ለማዳበሪያ ግዥ የሚሆን ተዘዋዋሪ ፈንድ/Revolving fund ፈቃድ ከማግኘት እንዲሁም ከታክስ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲቻል የቋሚ ኮሚቴውን ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡

 የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው የውይይትና የጉብኝት መርሐ ግብር ላይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ፣ ሦስት የንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ 19 አባላት እና ሰባት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ባለሞያዎች ተገኝተዋል፡፡

           ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው፡፡