አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14/2015 ዓ.ም (ኢግሥኮ) ፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) የአርሶ አደሮች፣ የባለሃብቶች እና የመንግሥት  ተቋማት ምርጥ ዘር አባዥዎችን የደረሱ ሰብሎች በተመጣጣኝ ዋጋ በመሰብሰብ አስረከበ፡፡

በኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎችና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ክፍሌ እንደተናገሩት፣ ኮርፖሬሽኑ እስከ ታህሳስ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ 90 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ አቅዶ ከ103 ሺህ ኩንታል በላይ የደረሰ ሰብል በመሰብሰብ ለደንበኞቹ አስረክቧል፡፡

በዋናነት ስንዴ፣ ገብስ እና ጎመን ዘር በኮምባይን ሀርቨስተር አጭደን፣ ወቅተን እና አጓጉዘን አስረክበናል ያሉት አቶ መንግሥቱ፣ ለኦሮሚያ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት፣ ለአየሁ እርሻ ልማት፣ ለአርሶ አደሮች እና ለኮርፖሬሽኑ ምርጥ ዘር ማባዣዎች አገልግሎቱ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

አክለውም የደረሱ ሰብሎች ሙሉ በሙሉ ተሰብስበው ጎተራ እስኪገቡ ድረስ የምርት መሰብሰቡን ሥራ እንደሚቀጥሉ አስታውቀው፣  በአጠቃላይ በዚህ ዓመት ለአርሶ አደሮች እና ሌሎች የሜካናይዜሽን አገልግሎት ፈላጊዎች 261 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ በ13 አጭዶ መውቂያ መሣሪያዎች እንዲሁም ምርትን ወደ አውድማ እና ጎተራ በሚያጓጉዙ 10 ገልባጭ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ እየተሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል።

የምርት መሰብሰብ አገልግሎቱ በአርሲ፣ ባሌ፣ ሸዋ እና ጎጃም አካባቢዎች በስፋት እየተሰጠ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መንግሥቱ፣ የምርት መሰብሰብ ሥራው ተረፈ ምርትን ለእንስሳት መኖ እንዲሆን በሚያስችል መልኩ በጥራት እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ ምርት ከመሰብሰብ ሥራ ጎን ለጎን በደንበኞች ጥያቄ መሰረት የእርሻ መሬት እያዘጋጀ ነው ያሉት አቶ መንግሥቱ፣ በዚህ ረገድ በዳውሮ ዞን ዴሳ ወረዳ የቅባት እህሎችን በማምረት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ለተሰማራ ልማታዊ ባለሃብት እየተዘጋጀ የሚገኘው 1 ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት ይጠቀሳል ብለዋል፡፡

አያይዘውም እስከ ህዳር 12/2015 ዓ.ም ድረስ 130 ሄክታር የሚሆን መሬት ለእርሻ በሚመች መልኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ የእርሻ መሣሪያዎችና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ በኮርፖሬሽኑ የታማሻሎ ምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት 300 ሄክታር መሬት በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የማሳ ዝግጅትን በተመለከተም የኢትዮ አግሪ ሴፍት አየሁ እርሻ ልማት 2 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ለማልማት ውል መገባቱን ያስታወቁት አቶ መንግሥቱ፣ የእርሻ መሣሪያዎችን የማጓጓዝ እና የማሰማራት ሥራ እየተከናወነ በመሆኑ በቅርቡ ሥራው እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

የምርት መሰብሰብ ሥራን እና ሌሎች ውል የተገባባቸውን የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎቶች በብቃት እንዲፈጸሙ ለማስቻል በአመራር ደረጃ በመስክ ተገኝቶ ሠራተኞችን በማበረታታት የተሻለ የሥራ ተነሳሽነት መፍጠር እንደተቻለም ገልጸዋል።

ግብርናን ለማዘመን የሜካናይዜሽን አገልግሎትን በስፋት ተደራሽ ማድረግ ይገባል የሚሉት አቶ መንግሥቱ፣ ከዚህ አኳያም ኮርፖሬሽኑ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማዕከልን ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ አዳዲስ ማዕከላትን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማቋቋም እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከሚሰጣቸው በርካታ አገልግሎቶች ውስጥ ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ የሚዘልቅ የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ተጠቃሽ ሲሆን፣ ተቋሙ ይህን አገልግሎት በመስጠት ለምርትና ምርታማነት እድገት እና ግብርናን ለማዘመን በሚደረገው ሀገራዊ እንቅስቃሴ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡