አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለተጠቃሚዎች የሚያቀርበውን ምርጥ ዘር በጥራትና በመጠን ለማሳደግ በኮንትራት ሰፋፊ እርሻዎች ከባለሃብቶች ጋር እየሰራ ነው።

የይስሃቅ ሳምሶን እርሻ ልማት እና የዱቄት ፋብሪካ ባለቤት አቶ ይስሃቅ ሳምሶን ከኮርፖሬሽኑ ጋር ምርጥ ዘር ማባዛት ከጀመሩ ሶስት ዓመት እንደሆናቸው ገልጸው፣ በዚህ ዓመት ከኮርፖሬሽኑ ኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር ውል በመግባት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር እና ጃራ ወረዳዎች 210 ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ዘር እያባዙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

” ኮርፖሬሽኑ ባለሞያዎችን እየላከ ድጋፍና ክትትል ስለሚደርግልን ምርታማነታችን ከፍ እንዲል አድርጓል” ያሉት አቶ ይስሃቅ፣ በትብብር መስራታቸው ምርታማነታቸውን በመጨመሩ ወደፊትም ከኮርፖሬሽኑ ጋር መስራት ምርጫቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አክለውም ሰፊውን አርሶ አደር ዘር በማባዛት ለመጥቀም እና በምላሹም ለዱቄት ፋብሪካቸው ግብዓት የሚሆን ምርት ከአርሶ አደሩ ለመሰብሰብ የዘር ብዜት ሥራ ውስጥ መግባታቸውን አብራርተዋል፡፡

ሌላኛው የቡላላ ዲኒቂቲ እርሻ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን ጸጋየ የተሻለ ዘር በማምረት መንግሥትን እና ሕዝብን ለመደገፍ በሚል ሃሳብ ዘር በማባዛት ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ጠቁመው፣ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ አሁን በኮርፖሬሽኑ ስር ከሚገኘው የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት ጋር ውል በመግባት ዘር እያባዙ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ በ2014/15 የመኸር ወቅት ከኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር ውል በመግባት በምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር እና ጎሎልቻ ወረዳዎች ከ1 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተለያዩ የሰብል ዝርያችዎችን በማባዛት ላይ ናቸው ።

የኮርፖሬሽኑ ባለሞያዎች ከእርሻ ሥራ ጀምሮ ምርት እስኪሰበሰብ ድረስ ከእኛ ጋር ናቸው ያሉት አቶ መኮንን፣ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመስራታቸው ትርፋማ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ በተጨማሪም ያባዙትን ምርት ኮርፖሬሽኑ በራሱ ትራንስፖርት እና ከረጢት እንደሚረከባቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት ከሌላው ጊዜ የተሻለ የዝናብ ሥርጭት መኖሩን የተናገሩት አቶ መኮንን፣ ሰብሉ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ጥራት ያለው ዘር አባዝተው ለኮርፖሬሽኑ ለማስረከብ እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ የኤልፎራ ነትሌ እርሻ ሥራ አስኪያጅ አቶ በኃይሉ ምትኩ በበኩላቸው፣ እንደ ሀገር ያለውን የበቆሎ ዘር እጥረት ለመቅረፍ እና በግብርናው ዘርፍ የራሳቸውን አስተዋጽዖ በማበርከት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ከኮርፖሬሽኑ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር 120 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ እያለሙ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ከኮርፖሬሽኑ ጋር የቆየ ግንኙኘት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ በኃይሉ፣ ከዚህ አኳያም ኮርፖሬሽኑን እንደራሳቸው ድርጅት እንደሚቆጥሩት ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የተለያዩ ሰብሎችን ዘር እያባዛን እንገኛለን ብለዋል።

ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ እና አግሮኬሚካሎችን ኮርፖሬሽኑ እንደሚያቀርብላቸው ገልጸው፣ የሜካናይዜሽን አገልግሎት በመስጠትም የኤልፎራ ነትሌ መሬትን ለእርሻ ዝግጁ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያደረገ ያለው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራ ለወገንም ሆነ ለሀገር በጣም ጠቃሚ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ወደፊትም ከኮርፖሬሽኑ ጋር መስራታችንን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

የኢቲኤም ጠቅላላ የግብርና ሥራ ባለቤት አቶ መስፍን ነጋሽ በበኩላቸው፣ የተለያዩ ሰብሎችን ምርጥ ዘር በብዛትና በጥራት በማባዛት ለአካባቢው አርሶ አደሮች ዘር ለማቅረብ የዘር ብዜት ሥራን በ1994 ዓ.ም መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኮርፖሬሽኑ የአሰላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አድአ ወረዳ በ76 ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ እና ሽንብራ እያባዙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

“ከኮርፖሬሽኑ ጋር እንደ ቤተሰብ ነው ተባብረን የምንሰራው” ያሉት አቶ መስፍን፣ የአሰላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከእርሻ ማሳ ዝግጅት ጀምሮ ምርት እስኪሰበሰብ ድረስ ክትትል እንደሚያደርግላቸው እና ለሚያጋጥማቸው ችግርም መፍትሔ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመስራታቸው ውጤታማ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ መስፍን፣ በ2007 ዓ.ም ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ በምርጥ ዘር ብዜት ሥራ የመንግሥት አጋዥ በመባል ሽልማት መቀበላቸውን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከራሱ እርሻዎች በተጨማሪ በኮንትራት አማካይነት በሰፋፊ የመንግሥትና የባለሃብት እርሻዎች እንዲሁም በአርሶ አደሮች ማሳዎች ላይ ዘር በማባዛት እና በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች እያቀረበ የሚገኝ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡

### ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!