የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን Ethiopian Agricultural Businesses Corporation

የኮርፖሬሽኑ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በሦስት ክልሎች በኮንትራት እርሻዎች ምርጥ ዘር እያባዛ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በሦስት ክልሎች በኮንትራት እርሻዎች የተለያዩ ሰብሎች ምርጥ ዘር እያባዛ ይገኛል፡፡

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አድማሱ አናጋው እንዳስታወቁት፣ ጽ/ቤቱ በተያዘው የ2014/15 የመኸር ወቅት በኮንትራት አባዥ ሰፋፊ የባለሃብት እርሻዎች፣ በመንግሥት የግብርና ተቋማት እና በአርሶ አደር ማሳዎች ላይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ እና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ፣ ስልጤ፣ ወላይታ፣ ሃድያ እና ሃላባ ዞኖች እንዲሁም በሲዳማ ክልል በድምሩ በስምንት ዞኖች በ2 ሺህ 34 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን ምርጥ ዘር በማባዛት ላይ ይገኛል።

በዋናነት የስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎ እና ቦለቄ ሰብሎችን ምርጥ ዘር እያባዛን ነው ያሉት አቶ አድማሱ፣ በዚህም 45 ሺህ 752 ኩንታል ዘር እንደሚገኝ ይገመታል ብለዋል፡፡

ዘር በከፍተኛ ጥንቃቄ ተመርቶ ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ የገለጹት አቶ አድማሱ፣ ከዚህ አኳያ ከማሳ መረጣ ጀምሮ ምርት ተሰብስቦ መጋዘን እስኪገባ ድረስ የክትትልና የጥራት ቁጥጥር ሥራዎችን በመስክ በመገኘት እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

የተለያዩ የሰብል ዘሮችን በማባዛት በመላ ሀገሪቱ እንደሚያሰራጩ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ በዚህ ወቅት እየተባዛ የሚገኘውን ምርጥ ዘር ጽ/ቤቱ በሀዋሳ ከተማ ባሉት ሁለት የዘር ማዘጋጃ ማሽኖች በማበጠርና በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

አክለውም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በሻሸመኔ ከተማ ባለው የሽያጭ ማዕከል አማካኝነት የአፈር ማዳበሪያ፣ አግሮኬሚካሎች እና የእንስሳት መድሃኒቶችን ለአርሶአደሩ በቅርበት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አርሶ አደሩ ከግብርና ምርምር የወጡ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን እንዲጠቀም ለማስቻል በተለያዩ አካባቢዎች የሰርቶ ማሳያ እና የአርሶ አደሮች በዓል በማዘጋጀት ዝርያዎቹን የማስተዋወቅ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

### ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

በኮርፖሬሽኑ የጎንዴ ኢተያ መስራች ዘር ማባዣ እርሻ ልማት እና በኮንትራት እርሻዎች ከ111 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11/2015 ዓ.ም (ኢግሥኮ) በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአሰላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አማካኝነት በጎንዴ ኢተያ መስራች ዘር ማባዣ እርሻ ልማት እንዲሁም በሰፋፊ የባለሃብትና የአርሶ አደር የኮንትራት እርሻዎች በዘር ከተሸፈነው 3 ሺህ 15 ሄክታር መሬት ከ111 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተገለጸ፡፡

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ የሺጥላ እንደገለጹት፣ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የራሱ እርሻዎች በሆኑት የጎንዴ ኢተያ እንዲሁም በሰፋፊ የባለሃብት እርሻዎች እና በአርሶ አደር ማሳ የ11 ሰብል ዓይነቶች 38 ዝርያዎች እየተባዙ ይገኛሉ፡፡

በ2014/15 የመኸር ወቅት 1 ሺህ 561 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 3 ሺህ 15 ሄክታር በዘር ለመሸፈን ተችሏል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ በዚህም ከ111 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡

የዘር ብዜት ሥራው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ እና አርሲ ዞኖች እየተካሄደ እንደሚገኝ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ በዋናነት በቢሾፍቱ፣ ወንጂ፣ ባቱ፣ በቆጂ እና ዴራ አካባቢዎች ባሉ ሰፋፊ እርሻዎችና ማሳዎች እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአበባ ደረጃ ያለ፣ ፍሬ መያዝ የጀመረ እና የደረሰ ሰብል አለ ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የተዘራው የስንዴ ሰብል በመድረሱ እየተሰበሰበ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በአሰላ ከተማ በሚገኘው የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዘር ማዘጋጃ ማሽን ለግብርና ምርምር ተቋማት፣ ለዘር አባዥዎች እና ለሌሎች ተጠቃሚዎች የዘር ብጠራ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አክለውም የአፈር ማዳበሪያ፣ የአግሮኬሚካሎች እና የዘር ሽያጭ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) ስር የሚተዳደረው የአሰላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ1973 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ በራሱ የመስራች ዘር ማባዣ እርሻ ጣቢያ እና በኮንትራት እርሻዎች እያባዛ ከሚገኘው ዘር በተጨማሪ ለአርሶ አደሩ፣ ለባለሃብቶች እና ለልማት ድርጅቶች የግብርና ማሳደጊያ ግብዓቶችን እያቀረበ ይገኛል፡፡

### ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

ኮርፖሬሽኑ ከአርዳይታ እርሻ ልማት ከ85 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ይጠብቃል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም. (ኢግሥኮ):- በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ስር ከሚተዳደሩት እርሻዎች አንዱ በሆነው የአርዳይታ ምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ከ85 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ፡፡

የአርዳይታ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ከበደ እንደገለጹት፣ በ2014/15 የመኸር ወቅት 3 ሺህ 70 ሄክታር መሬት በቅድመ መስራች፣መስራች እና የተመሰከረለት ዘር ደረጃዎች መሸፈን ተችሏል፡፡

ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ 360 ሄክታር በስንዴ፣ 612 ሄክታር በጎመን ዘር፣ 67 ሄክታር በገብስ እና 31 ሄክታር በባቄላ ዝርያዎች መሸፈኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ሰብል በእሸት እና አበባ ደረጃ ይገኛል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ የሰብሎቹ ሁኔታ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ የተለየ ተፈጥሮአዊ ችግር ካላጋጠመ በስተቀር ያቀዱትን ከ85 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያሳኩ አስታውቀዋል፡፡

የአርዳይታ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በቅድመ መስራች፣ መስራች እና የተመሰከረለት የዘር ደረጃ 33 የስንዴ፣ ዘጠኝ የገብስ፣ አንድ የባቄላ እና አንድ የጎመን ዘር ዝርያዎችን እያባዛ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ለአካባቢው ነዋሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን እና ትብብሮችን እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ፍቃዱ፣ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ዘር ከመሸጫ ዋጋ አምስት በመቶ ቅናሽ በማድረግ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በየዓመቱ በአረም እና ምርት መሰብሰቢያ ወቅት ከ800 እስከ 1000 ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል እንደሚፈጠርም አስረድተዋል፡፡

ተረፈ ምርትን ወይም የሰብል ገለባን በማኅበር ለተደራጁ የአጎራባች ቀበሌ ሥራ አጥ ወጣቶች በመስጠት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ያለውን ድጋፍም አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ክሊኒክ ለአካባቢው ነዋሪዎች በቅናሽ ዋጋ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና እርዳታ፣ ነጻ የማዋለድ እና የአምቡላንስ አገልግሎት ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑንም አክለው አስታውቀዋል፡፡

የአርዳይታ ምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ኮርፖሬሽኑ በስሩ ካሉት እርሻዎች መካከል በስፋት ትልቁ ሲሆን፣ መገኛውም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ አሳሳ ወረዳ ነው፡፡

### ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

ኮርፖሬሽኑ የምርጥ ዘር አቅርቦትን ለማሳደግ ከባለሃብቶች ጋር እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለተጠቃሚዎች የሚያቀርበውን ምርጥ ዘር በጥራትና በመጠን ለማሳደግ በኮንትራት ሰፋፊ እርሻዎች ከባለሃብቶች ጋር እየሰራ ነው።

የይስሃቅ ሳምሶን እርሻ ልማት እና የዱቄት ፋብሪካ ባለቤት አቶ ይስሃቅ ሳምሶን ከኮርፖሬሽኑ ጋር ምርጥ ዘር ማባዛት ከጀመሩ ሶስት ዓመት እንደሆናቸው ገልጸው፣ በዚህ ዓመት ከኮርፖሬሽኑ ኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር ውል በመግባት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር እና ጃራ ወረዳዎች 210 ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ዘር እያባዙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

” ኮርፖሬሽኑ ባለሞያዎችን እየላከ ድጋፍና ክትትል ስለሚደርግልን ምርታማነታችን ከፍ እንዲል አድርጓል” ያሉት አቶ ይስሃቅ፣ በትብብር መስራታቸው ምርታማነታቸውን በመጨመሩ ወደፊትም ከኮርፖሬሽኑ ጋር መስራት ምርጫቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አክለውም ሰፊውን አርሶ አደር ዘር በማባዛት ለመጥቀም እና በምላሹም ለዱቄት ፋብሪካቸው ግብዓት የሚሆን ምርት ከአርሶ አደሩ ለመሰብሰብ የዘር ብዜት ሥራ ውስጥ መግባታቸውን አብራርተዋል፡፡

ሌላኛው የቡላላ ዲኒቂቲ እርሻ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን ጸጋየ የተሻለ ዘር በማምረት መንግሥትን እና ሕዝብን ለመደገፍ በሚል ሃሳብ ዘር በማባዛት ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ጠቁመው፣ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ አሁን በኮርፖሬሽኑ ስር ከሚገኘው የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት ጋር ውል በመግባት ዘር እያባዙ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ በ2014/15 የመኸር ወቅት ከኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር ውል በመግባት በምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር እና ጎሎልቻ ወረዳዎች ከ1 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተለያዩ የሰብል ዝርያችዎችን በማባዛት ላይ ናቸው ።

የኮርፖሬሽኑ ባለሞያዎች ከእርሻ ሥራ ጀምሮ ምርት እስኪሰበሰብ ድረስ ከእኛ ጋር ናቸው ያሉት አቶ መኮንን፣ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመስራታቸው ትርፋማ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ በተጨማሪም ያባዙትን ምርት ኮርፖሬሽኑ በራሱ ትራንስፖርት እና ከረጢት እንደሚረከባቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት ከሌላው ጊዜ የተሻለ የዝናብ ሥርጭት መኖሩን የተናገሩት አቶ መኮንን፣ ሰብሉ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ጥራት ያለው ዘር አባዝተው ለኮርፖሬሽኑ ለማስረከብ እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ የኤልፎራ ነትሌ እርሻ ሥራ አስኪያጅ አቶ በኃይሉ ምትኩ በበኩላቸው፣ እንደ ሀገር ያለውን የበቆሎ ዘር እጥረት ለመቅረፍ እና በግብርናው ዘርፍ የራሳቸውን አስተዋጽዖ በማበርከት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ከኮርፖሬሽኑ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር 120 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ እያለሙ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ከኮርፖሬሽኑ ጋር የቆየ ግንኙኘት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ በኃይሉ፣ ከዚህ አኳያም ኮርፖሬሽኑን እንደራሳቸው ድርጅት እንደሚቆጥሩት ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የተለያዩ ሰብሎችን ዘር እያባዛን እንገኛለን ብለዋል።

ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ እና አግሮኬሚካሎችን ኮርፖሬሽኑ እንደሚያቀርብላቸው ገልጸው፣ የሜካናይዜሽን አገልግሎት በመስጠትም የኤልፎራ ነትሌ መሬትን ለእርሻ ዝግጁ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያደረገ ያለው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራ ለወገንም ሆነ ለሀገር በጣም ጠቃሚ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ወደፊትም ከኮርፖሬሽኑ ጋር መስራታችንን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

የኢቲኤም ጠቅላላ የግብርና ሥራ ባለቤት አቶ መስፍን ነጋሽ በበኩላቸው፣ የተለያዩ ሰብሎችን ምርጥ ዘር በብዛትና በጥራት በማባዛት ለአካባቢው አርሶ አደሮች ዘር ለማቅረብ የዘር ብዜት ሥራን በ1994 ዓ.ም መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኮርፖሬሽኑ የአሰላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አድአ ወረዳ በ76 ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ እና ሽንብራ እያባዙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

“ከኮርፖሬሽኑ ጋር እንደ ቤተሰብ ነው ተባብረን የምንሰራው” ያሉት አቶ መስፍን፣ የአሰላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከእርሻ ማሳ ዝግጅት ጀምሮ ምርት እስኪሰበሰብ ድረስ ክትትል እንደሚያደርግላቸው እና ለሚያጋጥማቸው ችግርም መፍትሔ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመስራታቸው ውጤታማ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ መስፍን፣ በ2007 ዓ.ም ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ በምርጥ ዘር ብዜት ሥራ የመንግሥት አጋዥ በመባል ሽልማት መቀበላቸውን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከራሱ እርሻዎች በተጨማሪ በኮንትራት አማካይነት በሰፋፊ የመንግሥትና የባለሃብት እርሻዎች እንዲሁም በአርሶ አደሮች ማሳዎች ላይ ዘር በማባዛት እና በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች እያቀረበ የሚገኝ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡

### ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!