የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2014 በጀት ዓመት ከ62 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ለተጠቃሚዎች አቅርቧል፡፡

በኮርፖሬሽኑ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ገብሬ እንደገለጹት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኮርፖሬሽኑ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ የአፈር ማዳበሪያ፣ የሰብል ተባይ ማጥፊያ አግሮኬሚካሎች እና ኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችን ከዓለም አቀፍ አቅራቢዎች በመግዛት ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ችሏል፡፡

በዚህ መሰረት ለ2014/15 የሰብል ዘመን የሚውሉ 61 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው 12 ሚሊዮን 876 ሺህ 620 ኩንታል ዩሪያ፣ ኤን ፒ ኤስ እና ኤን ፒ ኤስ ቢ የአፈር ማዳበሪያዎች ለአርሶ አደሮች፣ ለከፊል አርብቶ አደሮች እና በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች መቅረቡን ነው ሥራ አስፈጻሚው ያስታወቁት፡፡

በተጨማሪም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ፈሳሽ እና ዱቄት አግሮኬሚካሎች እና 3 ሺህ 870 የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎች ለተጠቃሚዎች ተደራሽ መደረጋቸውን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም 58 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው የእንስሳት መድሃኒቶች ሽያጭ መከናወኑንም ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የአፈር ማዳበሪያ እና አግሮኬሚካሎች በኮርፖሬሽኑ መጋዘኖች እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ሰለሞን፣ ተጠቃሚዎች ግብዓቶችን በመግዛት ምርትና ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይም ተጨማሪ ደረጃቸውን የጠበቁ የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች በብዛት እንደሚቀርቡ አመልክተው፣ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የአግሮኬሚካሎች ግዥ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት በኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ለተጠቃሚዎች ከቀረቡ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች ግብዓት ሽያጭ፣ ከአገልግሎት ክፍያ እና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ከ3 ቢሊዮን 416 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም ሥራ አስፈጻሚው አክለው አስታውቀዋል፡፡                                                              ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

አቶ ሰለሞን ገብሬ
የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ