ከኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) ጋር ውል ገብተው ምርጥ ዘር እያባዙ ለሚገኙ ባለሃብቶች ኮርፖሬሽኑ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገለጹ፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ይህን የገለጹት፣ በምስራቅ ባሌ ዞን  በኮንትራት እርሻ ለኮርፖሬሽኑ የምርጥ ዘር እያባዙ ከሚገኙ ባለሃብቶችና የባለድርሻ አካላት ጋር  በቢሾፍቱ ያቱ ሆቴል ግንቦት 28/2014 ዓ.ም. በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡ “እናንተ ዘር የምታባዙት ለእኛ በመሆኑ ከራሳችን እርሻ ለይተን አናያችሁም” ያሉት አቶ ክፍሌ፣ ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ እና በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ነን ብለዋል፡፡ ባለሃብቶቹ በበኩላቸው ምርጥ ዘር የማባዛት ሥራን ከኮርፖሬሽኑ ጋር በትብብር እየሰሩና በተቋሙም ድጋፍ እየተደረገላቸው ስለመሆኑ አስታውሰው፣ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ አክለውም በአፈር ማዳበሪያ፣ በመስራች ዘር እና አግሮኬሚካሎች አቅርቦት ላይ ያጋጠሙ ችግሮች እንዲስተካከሉ እንዲሁም የሰብል ዝርያዎች ምርታማነት እየቀነሰ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ አዳዲስ የተሻሻሉ የሰብል ምርጥ ዘሮች እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡

 የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከባለሃብቶች ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ የተጠየቁ የግብርና ግብዓቶችን በቀጣይ ጊዜያት እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። በኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽን ዐቢይ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ በመድረኩ ባቀረቡት ገለጻ፣ ኮርፖሬሽኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን የምርጥ ዘር አቅርቦት እየሸፈነ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ከዚህ ውስጥ ኮርፖሬሽኑ አብዛኛውን ዘር በሰፋፊ የመንግሥት እና ባለሃብቶች እርሻዎች እንዲሁም በአርሶ አደር ማሳ ላይ በትብብር በማምረት ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ አኳያ በዘንድሮ የሰብል ዘመን ኮርፖሬሽኑ ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው ምርጥ ዘር በብድር ለባለሃብቶች መስጠቱን እንዲሁም የሞያና ሌሎች ድጋፎችን ማድረጉን በኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያ ምርጥ ዘርና ደን ውጤቶች አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘነበ ወልደሥላሴ ተናግረዋል። የኮፈሌ ቅ/ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ቡሽራ መሐመድ በበኩላቸው፣ ቅርንጫፉ ከምርጥ ዘር አባዥ ባለሃብቶች ጋር በመተባበር በመጪው የመኸር ወቅት 5 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በዘር በመሸፈን ከ131 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለማምረት አቅዶ አየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በኮንትራት እርሻ በተለያዩ አካባቢዎች በባለሃብቶች መሬት ከሚያባዛው ምርጥ ዘር ውስጥ  በምስራቅ ባሌ ዞን የሚያባዛው ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አቶ ቡሽራ ጠቁመዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የምስራቅ ባሌ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ እስማኤል ባስተላለፉት መልእክት፣ ኮርፖሬሽኑ በዞኑ ለሚያደርገው የግብርና ልማት በጋራ ከማቀድ ጀምሮ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀው፣ በዞኑ ያለውን የመስኖ ልማት በመጠቀም ለቆላማ አካባቢዎች ተስማሚ የሆኑ ምርጥ ዘር የማባዛት ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ አመላክተዋል። በመድረኩ ስለ ምርጥ ዘር አመራረት፣ አዘገጃጀትና ሥርጭት፤ የዘር ጥራት ቁጥጥር፣ መርሆዎችና ሂደት እንዲሁም የሀገሪቱ የምርጥ ዘር ፖሊሲ፣ ህግና ደንብን አስመልከቶ በባለሞያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ የኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባዘጋጀው በዚህ የግማሽ ቀን የውይይት መድረክ ላይ የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ባለሞያዎች፤ የምስራቅ ባሌ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ፣ የዞኑ የግብርና እና ኢንቨስትመንት ጽ/ቤት ሓላፊዎች፤ በምርጥ ዘር ብዜት የተሰማሩ ድርጅቶች እና ማህበራት እንዲሁም የአርዳይታ እና አጋርፋ የግብርና ቴክኒክና ሞያ ማሠልጠኛ ኮሌጆች ተገኝተዋል፡፡ በመድረኩ ማጠቃለያም በ2013/14 የምርት ዘመን ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመተባበር በምስራቅ ባሌ ዞን በኮንትራት እርሻ በምርጥ ዘር ብዜት የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ የዘር አባዦችና የባለድርሻ አካላት የምስጋናና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶአቸዋል። የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በራሱ እርሻዎች፣ በሰፋፊ የመንግሥት እና ባለሃብት እርሻዎች እንዲሁም በአርሶ አደር ማሳ ላይ ምርጥ ዘርን በጥራት እና በብዛት በማባዛት ለተጠቃሚዎች እያሰራጨ የሚገኝ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡

ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!