የግብርና ሚኒስትሩና የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ የአሰላ ቅርንጫፍ ጎንዴ ኢተያ እርሻ ጣቢያዎችን ነሐሴ 16/2013 ዓ.ም ጎበኙ።

በጉብኝቱ ወቅት የተገኙት የኢፌዲሪ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን፣ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ግርማ አመንቴ እና የኮርፖሬሽኑ የቦርድ አባላት አሰላ ቅርንጫፍ ጎንዴ ኢተያ እርሻ ጣቢያዎች ላይ የተዘሩ የጤፍ፣ ስንዴ፣ ባቄላ፣ ጎመን፣ ተልባ፣ ሽምብራና በቆሎ የሰብል ዘሮችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

 በተጨማሪም የአሰላ ቅርንጫፍ የምርጥ ዘር መጋዘንና የዘር ማበጠሪያ (ማዘጋጃ) ማሽን ጎብኝተዋል።

 ከጉብኝቱ በኋላ በተደረገ ውይይት አስተያየታቸውን የሰጡት የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ግርማ አመንቴ በተመለከቱት የልማት ሥራ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አክለውም ኮርፖሬሽኑ ለምርጥ ዘር ማባዣ የሚውል ተጨማሪ መሬት ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው፣ በተለይም የአርሶ አደሩን ማሳ ለዘር ማባዣነት ለመጠቀም የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ የኮንትራት እርሻ የአሠራር ስምምነት (contractual farming system) መተግበር እንዳለበት አስታውቀዋል።

 በዚህ የአሠራር ስምምነት አርሶ አደሩ የእርሻ መሬቱን ተጠቅሞ ኮርፖሬሽኑ የሚያቀርብለትን ምርጥ ዘር ካባዛ በኋላ ኮርፖሬሽኑ ምርቱን መልሶ ስለሚገዛው የበርካታ ሰብል ዝርያዎችን ዘር በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ማባዛት እንደሚቻል አስረድተዋል።

በአስተያየታቸው ማጠቃለያም የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ኮርፖሬሽኑ የተሰጠውን ተልዕኮ ይበልጥ መወጣት እንዲችል ከአርሶ አደር ጋር በሚደረግ የኮንትራት እርሻ ስምምነት፣ በአፈር ማዳበሪያ ግብይትና ፋይናንስ ሥርዓት ፖሊሲ፣ በሚወገድ ማዳበሪያ፣ በፋይናንስ እና አፋጣኝ መፍትሔ በሚያስፈልጋቸው ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የግብርና ሚኒስቴር እገዛ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

 የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በበኩላቸው በተመለከቱት ሁሉ መደሰታቸውን ገልጸው፣ ኮርፖሬሽኑ የዘር ብዜት ሥራውን ይበልጥ ማስፋትና ማሳደግ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

አያይዘውም ኮርፖሬሽኑ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ለመፍታት የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ እንዲያዘጋጅ ጠይቀዋል።

 ይህን በተመለከተም የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ግርማ አመንቴ በቅርቡ አንድ የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ለኮርፖሬሽኑ ማኔጅመንት የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።  በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአሰላ ቅርንጫፍ ጎንዴ ኢተያ እርሻ ጣቢያዎች በ2013/14 የሰብል ዘመን የመኸር ወቅት በ389 ሄክታር መሬት ላይ በ10 ሰብሎች 36 የተለያዩ ቅድመ መስራች እና መስራች ዝርያዎች ተዘርተዋል።